ጥሎ ማለፍ | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፈዋል

የኢትዮጵያ ጥሎማለፍ 2ኛ ዙር ጨዋታዎች መደረግ ሲጀምሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜ ተሸጋግረዋል፡፡

08:30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከዚህ አለም በሞት የተለየው አሰግድ ተስፋዬን በአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማሰብ በተጀመረው ጨዋታ የድሬዳዋ ከተማ አባላት አሰግድን የሚዘክር ቲሸርት በመልበስ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት፡፡

ጎል ባልተቆጠረበት እና እጅግ የተቀዛቀዘ በነበረው የመጀመርያ አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩ ሲሆን የሚቆራረጡ እንቅስቃሴዎች የጨዋታው አካል ነበሩ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥሮ አሸንፎ መውጣት ችሏል፡፡

በ67ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ማድረግ ሲችል ተቀይሮ የገባው ኮኔ ብራሂማ በ75 እና 80ኛ ደቂቃዎች አከታትሎ አስቆጥሯል፡፡ ለጎሎቹ መቆጠር በኃይሉ አሰፋ ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የአይቮሪያዊው አጥቂ አጨራረስም ግሩም ነበር፡፡

በመቀጠል የተገናኙት መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ነበሩ፡፡ መከላከያ በለጠ ገብረ ኪዳንን ወደ ብሔራዊ ቡድን በመሸኘቱ ፣ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ውበቱ አባተን በቅጣት በማጣቱ ሁለቱም ቡድኖች በረዳት አሰልጣኞቻቸው እየተመሩ ነበር ጨዋታቸውን ያከናወኑት፡፡

ባዬ ገዛኸኝ በ9ኛው ደቂቃ መከላከያን ቀዳሚ ሲያደርግ በ21ኛው ደቂቃ ምሰጋናው ወልደዮሀንስ ሀዋሳን አቻ አድርጓል፡፡ በ38ኛው ደቂቃ የቀድሞው የመከላከያ አማካይ ፍሬው ሰለሞን በፈፀመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ከእረፍት መልስ አማካዩ ሳሙኤል ሳሊሶ በ68ኛው ደቂቃ መከላከያን ለድል ያበቃችውን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመከላከያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውድድሩ እስከ ሰኞ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል መርሀ ግብሩ ይህንን ይመስላል፡-

[table id=362 /]