ካሜሩን በ2019 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች አርብ ምሽት ሱዳን እና ግብፅ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምረዋል፡፡ በምድብ አንድ የምትገኘው ሱዳን ማዳጋስካርን አስተናግዳ ባልተጠበቀ መልኩ 3-1 ስትሸነፍ በምድብ አምስት ሊቢያ ሲሸልስን 5-1 ረታለች፡፡
ኦባያድ ከተማ በሚገኘው አል ኦባያድ ስታዲየም የተደረገው የሱዳን እና ማዳጋስካር ጨዋታ ያልተጠበቀ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በጨዋታው ጅማሮ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ማዳጋስካሮች በ15ኛው ደቂቃ የዞትሳራ ራንድሪያምቦሎሎና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስን በአግባቡ የተጠቀመው አምበሉ ፋኔቫ አንድሪያሲማ ግብ መሪነቱን ጨብጠዋል፡፡ ሱዳን የአቻነት ግብ ለማግኘት አልፎ አልፎ የግብ እድሎችን ከመፍጠር የዘለለ ግብ ማስቆጠር አልቻለችም፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ማዳጋስካሮች በ62ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፉበት ወሳኝ ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል፡፡ ለአልጄሪያው ዩኤስኤም አልጀር የሚጫወተው አጥቂው ካርሎስ አንድሪያማሂትሲኖሮ እራሱ ላይ የተሰራው ጥፋት ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ በአል ኦቦያድ ስታዲየም የተገኘውን የሱዳን ደጋፊ ዝም አስኝቷል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ በመጀመሪያው አጋማሽ ባላ ጋብርን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አታሂር አል ጣሂር ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ሱዳኖችን ወደ ጨዋታው የመለሰች ብትሆንም በፈረሰንይ የሚጫወተው አንድሪያሲማ በ83ኛው ደቂቃ አህመድ አብደልአዚም መረብ ላይ ያስቆጠራት ሶስተኛ ማዳጋስካር በምድብ መክፈቻ ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብን ከሜዳዋ ውጪ እንድታገኝ አስችሏል፡፡ በጨዋታው ፓውሊን ቮቪ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ከማዳጋስካር ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑን በውጪ ሃገራት ሊጎች በሚጫወቱ ተጫዋቾች ያወቀሩት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ኒኮላስ ዱፑስ ሱዳን ላይ ያልተጠበቀ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ሱዳን ያለፉትን አመታት በእግርኳስ ፌድሬሽኑ ውስጥ በተነሱ አስተዳደራዊ ችግሮች ስትታመስ ቆይታለች፡፡ ቡድኑን ለረጅም ግዜያት የመሩት አሰልጣኝ መሃመድ አብደላ ማዝዳ ከ2012 ወዲህ ቡድኑን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ተስኗቸዋል፡፡ በምሹቱም ጨዋታ ላይ ማዝዳ ልምድ ያላቸውን የአል ሜሪክ እና አል ሂላል ተጫዋቾችን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አለማካተታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡
ሊቢያ ሲሸልስን 5-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ማጣሪውን በድል ጀምራለች፡፡ ግብፅ ፔትሮስፖርት ስታዲየም ላይ በተደረገው ጨዋታ ከጅማሮው አንስቶ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ የበላይነት የነበራት ሊቢያ ነበረች፡፡ በመጀመሪያው 45 በአኒስ ሳልቶ፣ አህመድ ቤንአሊ (በፍፁም ቅጣት ምት) እንዲሁም ሃምዱ አል መስሪ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሊቢያ 3-0 መምራት ችላለች፡፡ ከእረፍት መልስ በ66ኛው ደቂቃ መሃመድ ዙባያ አራተኛውን ግብ ሲያክል በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ከኢትዮጵያዊው ሳላዲን ሰዒድን ተከትሎ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ከሱዳናዊው በክሪ አል መዲና ጋር በእኩል አምስት ግቦች ሁለተኛ የሆነው የአል አሃሊ ትሪፖሊው ሙኤድ ኤላፊ የሊቢያን አምስተኛ ግብ በ84ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ በጨዋታ መገባደጃ ላይ ለርዋ ኮራሊ ሲሸልስን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነች የማስተዛዘኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
በርከት ያሉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ከቀትር ጀምሮ ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡ በምድብ 6 ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ሴራሊዮን እና ኬንያ ፍሪታውን ላይ ሲጫወቱ ናይጄሪያ ከደቡብ አፍሪካ፣ ማሊ ከጋቦን፣ ኮትዲቯር ከጊኒ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ ከኮንጎ ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምትን አግኝቷል፡፡ የምስራቅ አፍሪካዎቹ ዩጋንዳ ኬፕ ቨርድን ስትገጥም ታንዛኒያ ሌሶቶን ታስተናግዳለች፡፡ ካሜሮን ከሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታ ኢትዮጵያዊያኑ ዳኞች ባምላክ ተሰማ፣ ሃይለራጉኤል ወልዳይ እና ጋቦን በቅርቡ ባስተናገደችው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ በረዳት ዳኝነት የተሳተፈው ተመስገን ሳሙኤል ይመሩታል፡፡ በገንዘብ እጦት ብሩንዲን ለመግጠም ቡጁምቡራ ለመጓዝ አቅም ያለነበረው የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ቡድን አንድ የሃገሪቱ ባለሃብት ያደረጉትን ድጋፍ ተከትሎ ዛሬ አርብ ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ከሰዓት ይካሄዳል፡፡
የአርብ ውጤት
ሱዳን 1-3 ማዳጋስካር
ሊቢያ 5-1 ሲሸልስ
የቅዳሜ ጨዋታዎች
14፡30 – ማላዊ ከ ኮሞሮስ (ካሙዙ ስታዲየም)
15፡00 – ብሩንዲ ከ ደቡብ ሱዳን (ፕሪንስ ሉዊ ራዋጋሶሬ ስታዲየም)
15፡00 – ካሜሮን ከ ሞሮኮ (ኦምኒስፖርትስ አማዱ አሂጆ)
15፡00 – ዛምቢያ ከ ሞዛምቢክ (ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም)
15፡30 – ቦትስዋና ከ ሞሪታንያ (ፍራንሲስታውን ስታዲየም)
16፡00 – ጊኒ ቢሳው ከ ናምቢያ (ኢስታዲዮ 24 ደ ሴቴምብሮ)
16፡00 – ኒጀር ከ ስዋዚላንድ (ስታደ ጄኔራል ኤስ.ኬ.)
16፡30 – ኬፕ ቨርድ ከ ዩጋንዳ (ፕራያ ስታዲየም)
16፡30 – ሴራሊዮን ከ ኬንያ (ሲያካ ስቲቨንስ ስታዲየም)
17፡00 – ናይጄሪያ ከ ደቡብ አፍሪካ (አክዋ ኢቦም ስታዲየም)
18፡00 – ኮትዲቯር ከ ጊኒ (ስታደ ደ ቦአኪ)
18፡00 – ቡርኪናፋሶ ከ አንጎላ (ኦገስት 4 ስታዲየም)
18፡30 – ዲ.ሪ. ኮንጎ ከ ኮንጎ ሪፐብሊክ (ኮምፕሌክስ ኦምኒስፖርትስ ስታደ ደስ ማርተርስ)
19፡00 – ማሊ ከ ጋቦን (26 ማርች ስታዲየም)
20፡00 – ታንዛኒያ ከ ሌሶቶ (ናሽናል ስታዲየም)
21፡00 – ሴኔጋል ከ ኤኳቶሪያል ጊኒ (ስታደ ሊዮፓርድ ሴዳር ሰንጋሆር)