ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን እሁድ ጋናን ኩማሲ ላይ በመግጠም ትጀምራለች፡፡ በዋሊያዎቹ የቡድን ስብስብ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ መካተት የቻለው የፋሲል ከተማው አብዱራህማን ሙባረክ እና ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ስለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት፣ ስለተጋጣሚ ቡድን ጋና እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
“ዝግጅቱ ብዙም አልከበደንም” አቡዱራህማን ሙባረክ
ወደ ብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ግዜ መጠራቱ
“ለብሄራዊ ቡድን መጠራት በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተጫዋች ስትሆን የመጨረሻው ነገር ለሃገርህ መጫወት ስትችል ነው፡፡ ጥሪ ሲደርስህ ምን ዓይነት ደስታ እንደሚፈጥርብህ መናገር ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ በጣም ነው ደስ ያለኝ የሆነ የተለየ ነገር ለመስራት እንዳቅድ እና እንዳልም ነው ያደረገኝ፡፡ እኔም ብዙ ነገር ነው እንዳስብ ያደረገኝ፡፡”
“በመጠራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ከነበረኝ አቅም በላይ ሁላ አውጥቼ ነው እንድጫወት ያደረገኝ፡፡ እኔም አቅም አለኝ እንድል ነው ያደረገኝ፡፡ ነገ ደግሞ ከአላህ ጋር የተሻለ ነገር ከእዚህም በላይ እሰራለው ብዬ አስባለው፡፡”
ዋሊያዎቹ ለጨዋታው ያላቸው ዝግጁነት
“ዝግጅታችን ጥሩ ነው፡፡ እኛም 9 ወር እየተጫወትን ስለነበረ ዝግጅቱ ብዙም አልከበደንም፡፡ ቀጥታ ወደ ቡድን የማቀናጀት እና የቡድን ስራ የመስራት ልምምዶችን ነው ማድረግ የቻልነው፡፡ በአጭር ግዜ እንደመሰባሰባችን ሳይሆን ረጅም ግዜ አብሮ እንደቆየ ቡድን ጥሩ ቅንጅት አለን፡፡ ከአላህ ጋር ጋናን እናሸንፋለን ብዬ አስባለው፡፡”
“እናሸንፋለን ብዬ አስባለው ፤ ባናሸንፍ እንኳን ነጥብ ይዘን እንወጣለን” አቤል ማሞ
ዋሊያዎቹ ለጨዋታው ያላቸው ዝግጁነት
“የተለየ የሚባል ዝግጅት ባናደርግም ውድድር ላይ የነበርን ተጫዋቾችን ስለሆነ ቡድኑ የያዘው እንዲሁም የነበረን አብሮነት ቆይታ አጭር ግዜ ስለሆነ ነው፡፡ የዝግጅት ወቅት አጭር ግዜ መሆኑን ተክትሎ አሰልጣኞቻችን የተጠቀሙበት ነገር ተጫዋቾችን ከውድድር ላይ እንደመጡ ማግኘታቸው ነው፡፡ በነበረው አጭር ግዜ ተጠቅመው ደግሞ የራሳቸውን ታክቲክ አሳይተውን በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገን ተስፋ ሰጪ የሆነ ነገር አሳይተናል፡፡ ዝግጅቱንም የሚገልፀው የወዳጅነት ጨዋታዎቹ ላይ ያሳየነው እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ በስሜትም ደረጃ የአዕምሮ ጥንካሬ እንዲኖረን ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በጥሩ መልኩ ነው ዝግጅት እያደረግን ያለነው፡፡”
ለጨዋታው ያለው ተነሳሽነት
“አብዛኛው ተጨዋች ከተወሰኑትን ውጪ ለዚህ መድረክ አዲስ ያልሆኑ ናቸው፡፡ ተነሳሽነቱ ላይ የሃገር እና የክብር ጉዳይ ስለሆነ እና ረጅም ግዜ ወስዶ የሚደረግ ውድድር ነው ስለዚህ እንደዚህ አይነት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዋጋ ከፍለህ ውጤትህን ስታሳምር የሚቀጥለው መንገድ የተመቻቸ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም የምድባችን ከባዱ ቡድን (ጋና) ነው፡፡ ይህንን ማለፍ ከቻልን ቀጣዮቹን ቡድኖችን በራስ-መተማመናችን ከፍ ብሎ እንድንገጥማቸው ያደርገናል ብዬ አስባለው፡፡”
ስለጋና ወቅታዊ ሁኔታ
“ከ30 ተጫዋቾች አብዛኞቹ በአውሮፓ ሊጎች እንደሚጫወቱ እናውቃለን፡፡ እኛ ጋር ስትመጣ ሁለት ተጫዋች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ያምሆኖ ግን ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች አለን እኛ ጋር፡፡ ምርጫው ድብልቅ ነው ከወጣቱም እንዲሁም ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች የተደረገ ነው፡፡ የጋናን ብሄራዊ ቡድን በምስልም ለማየት እንደሞከርነው የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ከዩጋንዳ ጋር ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች አይተናል፡፡ እኛም ዩጋንዳን ገጥመን ያለውን ነገር አይተናል፡፡ በጨዋታው የተሻለ ነገር ለመስራት ያገኘናቸውን መረጃዎች ይረዱናል፡፡ ከእግዛቢሄር ጋር ተሸንፎ የሚገባ ቡድን የለንም ሁሌም ለማሸነፍ ነው የምንገባው ምክንያቱም ሁሉም ተጫዋች ያለበት ወቅታዊ ደረጃ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ከሃገር ውስጥም ይሁን ከውጪ ሃገር ቡድኖች ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ነው ያሳየነው፡፡ እናሸንፋለን ብዬ አስባለው ባናሸንፍ እንኳን ነጥብ ይዘን እንወጣለን፡፡”