በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ሲደረጉ ከጋና፣ ሲዬራሊዮን እና ኬንያ ጋር በምድብ 6 የተደለደሉት ዋልያዎቹ ወደ ኩማሲ ተጉዘው ከጋና ጥቋቁር ከዋክብት ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ጨዋታውን በተመለከተም የጋና ብሔራዊ ቡድን አባላት እና የቀድሞ ከዋክብት አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
በኦምና ታደለ እና ሳሙኤል የሺዋስ
የጋና ብሄራዊ ቡድንን ለሁለተኛ ግዜ በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ክዌሲ አፒያ ደጋፊዎች ወደ ባባ ያራ ስፖርትስ ስታዲየም እንዲመጡ ተማፅነዋል፡፡ እንደሱፐርስፖርት ዘገባ ከሆነ አሰልጣኝ አፒያ ከሶስት አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ጋና ወደ ኩማሲ ተመልሶ ለምታደርገው ጨዋታ ደጋፊዎች በብዛት ወደ ስታዲየሙ እንዲመጡ ይፈልጋሉ፡፡
“እሁድ ኢትዮጵያን በምንገጥምበት ጨዋታ ጋናዊያን ከጎናችን ሆነው እንዲያበረታቱን ተንበርክኬ እማፀናለው፡፡ እኛ ምንፈልገው ሁሌም ለጋና መልካሙን ነው” ብለው የቀድሞ የሱዳኑ አል ካርቱም ዋታኒ ዋና አሰልጣኝ፡፡ የጋና እግርኳስ ማህበር ደጋፊዎች ለጨዋታው ለመሳብ የስታዲየም መግቢያ ትኬቶችን ዋጋ በእጅጉ የቀነሰ እንዲሆን አድርጓል፡፡
አፒያ አክለው የአራት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኖቹ ተስጥኦ ያላቸው ተጫዋቾች በብዛት መገኘታቸውን ተክተሎ ተጫዋቾቹን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስቡ አስረድተዋል፡፡ “ተስእጦ ያለቸው ብዙ ተጫዋቾች በጋና አሉን፡፡ እኔም በቻልኩት መጠን ተጫዋቾቹን ለመጠቀም እና በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ለእያንዳንዱ ቦታ ውድድር እንዲኖር እፈልጋለው፡፡”
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ዋና ፀሃፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሱፐርስፖርት በሰጡት አስተያየት ዋሊያዎቹ ቢያንስ አንድ ነጥብን ከእሁዱ ጨዋታ ማሳካት እንደሚችሉ አምነዋል፡፡ “የመጀመሪያ ጨዋታችን በጣም ወሳኝ ነው ምክንያቱም ጋና ጥሩ ቡድን ስለሆነ፡፡ ከጋና ጋር አቻ ከተለያየን ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋችን ብሩህ እየሆነ ይመጣል፡፡ በጋና ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ከቻልን በቡድናችን ውስጥ መልካም የሆነ ስሜትን ያመጣል፡፡ ስለዚህም ጨዋታውን ለማሸነፍ አሊያም አንድ ነጥብ ለመውሰድ ከጨዋታው እንሞክራለን” ብለዋል፡፡
የቡድኑ አምበል የሆነው አሳሞአህ ግያን ከዩናይትድ አረብ ኢመሬትሱ ክለብ አል ኤይን ወደ ቻይናው ሻንጋይ ሼኑዋ በውሰት ውል ተዘዋውሮ የውድድር ዓመቱን ያሳለፈ ሲሆን ባለፉት 4 ወራት በተደጋጋሚ ባጋጠመው የጉልበት እና የቁርጭምጭሚት ጉዳት በበርካታ ጨዋታዎች መሰለፍ አልቻለም ነበር። ግያን ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ከተቀላቀለ በኋላ መጀመሪያ ላይ ለብቻው ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲሰራ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከቡድኑ ጋር ሙሉ ልምምዱን እያደረገ ይገኛል።
የ31 ዓመቱ አጥቂም “አሁን ሁሉም ነገር ጥሩ ነው። ጥሩ ስሜት እየተሰማኝ ነው። ለጨዋታውም ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ሆኜ እየጠበቅኩኝ ነው፤” ሲል ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታው መዘጋጀቱን ገልጿል። ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ በብሔራዊ ቡድን ማሊያ 50ኛ ግቡን ለማስቆጠር ተስፋ ያደረገ ሲሆን ጥቋቁር ኮዋክብቱ ዋሊያዎቹን እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ መሆኑንም ተናግሯል።
“ጨዋታው ኩማሲ ላይ መደረጉ ጥሩ ነው። እዚህ ከተጫወትን ረጅም ጊዜ ሆኖናል፤ በኩማሲ ህዝብ ፊት ላይ ፈገግታን ለማየትም የማናደርገው ነገር አይኖርም። ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ወደፊት ለሚኖሩን ጨዋታዎችም በራስ መተማመናችን እንዲጨምር የሚያደርግ ነው። ሙሉ በሙሉ በማጥቃት መጫወት ይኖርብናል፤ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ አያገኙም፤” ሲል ነው ሃሳቡን የተናገረው።
የእንግሊዙ ዌስትሃም ተጫዋች እና የጋና ብሔራዊ ቡድን ምክትል አምበል የሆነው አንድሬ አይው በአንፃሩ ጨዋታው ወሳኝ እንደሆነ እና ትልቅ ግምት እንደሚሰጡትም ተናግሯል። በ2018ቱ የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ኩማሲ ላይ አድርገው አቻ በመውጣታቸው አሁን ግብፅ እና ዩጋንዳን ተከትለው በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ መገደዳቸውን አስታውሶ በዚህ ጨዋታም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተናግሯል።
“አላማችን በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆን ነው። ይህንንም ለማሳካት የመጀመሪያውን ጨዋታ በሜዳችን በማሸነፍ በጥሩ መንፈስ ማጣሪያውን መክፈት አለብን። ከኢትዮጵያ 3 ነጥብ ማግኘት ግዴታችን ነው፤” ሲል ሀሳቡን ገልጿል።
ለጋና ብሄራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራው ለቱርኩ አላንያስፖር የሚጫወተው አማካይ አይዛክ ሳኬይ በበኩሉ ጥቋቁር ከዋክብቱ ጨዋታውን እንደሚያሸንፍ ተናግሮ የኩማሲ ህዝብም ወደ ስታዲየም በመምጣት ቡድኑን እንዲያበረታታ ጥሪ አድርጓል።
“ከበርካታ ጋናውያን የሞራል ድጋፍ እያገኘን ነው፤ እሁድም ደጋፊዎቻችን ወደ ስታዲየም በመምጣት ኢትዮጵያን እንድናሸንፍ እንደሚደግፉን አልጠራጠርም። እሁድ ማሸነፍ ለእኛ እጅግ አስፈላጊያችን ነው። ለደጋፊዎቻችንን እና ጋናውያንን በሙሉ ኢትዮጵያን በማሸነፍ 3 ነጥብ እንደምናሳካ ከወዲሁ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፤” ሲል ሀሳቡን አስተላልፏል።
የቀድሞ የጋና ብሄራዊ ቡድን አጥቂ አውገስቲን አሂንፉል ኢትዮጵያን አሳምኖ ማሸነፍ ለጥቋቁር ከዋክብቶቹ ግዴታ እንደሆነ የጋናሶከርኔት ድህረ-ገፅ አስነብቧል፡፡
አሂንፉል ጋና በእሁዱ ጨዋታ ከኢትዮጵያ የተሻለ ጨዋታ ማሳየት እንደሚገባት ጨምሮ ገልጿል፡፡ “ኢትዮጵያዎች ከእኛ ነጥብ ለመውሰድ እና ያልተጠበቀ ውጤት ለማስመዝገብ ወደ ኩማሲ ቢመጡ የሚገርም አይሆንም፡፡ ስለዚህም በእኔ አስተሳሰብ የሚፈልጉትን ጨዋታ እንዳይጫወቱ ማገድ እና ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት መቻል አለብን፡፡”
ጋና ኩማሲ ባባ ያራ ስፖርትስ ስታዲየም ላይ ጨዋታ ካደረገች ሶስት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሶስት አመታት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዩጋንዳ ጋር 1 አቻ ከተለያየች ወዲህ ኩማሲ እና የጋና ብሄራዊ ቡድን ተለያይተው ቆይተዋል፡፡ በጨዋታው ወቅት በስታዲየሙ የተገኘው ደጋፊ በ2014ቱ የአለም ዋንጫ ብዙ ተጠብቆ ከምድብ የተሰናበተው ቡድናቸው ላይ ቅሬታውን እና ተቃውሞውን አሳይቷል፡፡ በሶስት አመታት ውስጥም አብዛኞቹን የሜዳ ላይ ጨዋታቸውን ታማሌ፣ ኢሲፖን፣ አክራ እና ታኮራዲ ላይ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
እንደአሂንፉል ገለፀ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የደጋፊዎችን ልብ ዳግም ለመሳብ ትልቅ ሃይል እንዳለው ያምናል፡፡ “ደጋፊዎችን ዳግም ማግኘት የሚቻለው በአሳማኝ ብቃት እና በአስደሳች ጨዋታ ተጋጣሚያችንን ማሸነፍ ስንችል ብቻ ነው፡፡”
ጨዋታው እሁድ ምሽት 12፡30 ላይ 40,528 ተመልካቾችን በወንበር የማስተናገድ አቅም ባለው ባባያራ ስፖርትስ ስታዲየም ሲደረግ ሴኔጋላዊው ዳኛ ማግዌቴ ንዲያዬ እና ረዳቶቻቸው ጨዋታውን የሚመሩ ይሆናል። ጨዋታው በዲኤስቲቪ ሱፐርስፖርት 3 ላይ ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ይጠበቃል።