ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች የጥሎ ማለፍ አሸናፊ ሆነ

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ አዳማ አበበ በቂላ ስቴዲድም ላይ ተካሂዶ ወላይታ ድቻ አዳማ ከተማን 2-1  በመርታት የዋንጫው አሸናፊ ሆኗል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ አሊሚራህ መሀመድ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል ፣ የአዳማ ከተማ ፕሬዝዳንት አቶ አለማየሁ ቱሉ ፣ የወላይታ ድቻ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሊሶ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በታደሙበትና ቁጥር በርከት ያለ የአዳማ ከተማ ስፖርት ቤተሰብ በተከታተለው ጨዋታ አስገራሚ  የመሸናነፍ ፉክክር  ተስተናግዶበታል፡፡ አዳማ ከተማ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስዶ ሲጫወት ወላይታ ድቻ በአንፃሩ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴአሳይቷል፡፡ መልካም የሚባል የተጨዋቾቹ ዲሲፒሊን የታየበት እና  በታዳጊዎች ላይ ቢሰራ በርካታ አቅም ያላቸው ተስፈኞችን ማግኘት እንደሚቻል የተስተዋለበት ጨዋታም ነበር፡፡

በግማሽ ፍፃሜው ወላይታ ድቻ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክን 2-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ፣ አዳማ ከተማ ደግሞ አ/አ ከተማን በመለያ ምቶች 4 – 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር ለፍፃሜው ጨዋታ የተገናኙት፡፡

ጨዋታው የፍፃሜ ጨዋታ እንደመሆኑ መጠን በሁለቱም በኩል ጨዋታው ሳቢና አዝናኝ ሆኖ ቢቀጥልም በሁሉም ረገድ ለማለት በሚያስችል መልኩ አዳማዎች ፍፁም የበላይ ነበሩ፡፡ በጎል ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ባለ ሜዳዎቹ አዳማዎች 22 ደቂቃ ላይ በዕለቱ ምርጥ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ያብስራ አክሊሉ በአንድ ሁለት ቅብብል በመግባት  ግሩም ጎል አስቆጥሮ አዳማን መሪ አደረገ።

ጨዋታ በአዳማ ብልጫ በቀጠለበት እንቅስቃሴ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው የወላይታ ዲቻው ምስክር መለሰ ወደ ጎል ያሻማውን በላይ ጌታቸው በራሱ ጎል ላይ አስቆጥሮ ድቻ አቻ በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ወላይታ ድቻ ተሽሎ የታየ ሲሆን በ47 ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮዽያ 17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በተከላካይ ስፍራ ሲጫወት የምናውቀው ኢዮብ አለማየሁ ከርቀት ግሩም ጎል አስቆጥሮ ድቻን መሪ አደረገ።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ከሚፈጥሩት የጎል ሙከራ ውጭ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚባል አጨዋወት በአዳማ ከተማ  ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ 72ኛው ደቂቃ ላይም አዳማዎች አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ፍ/ቅ/ምትን ሳይጠቀሙበት ከመቅረታቸው በተጨማሪ ሌሎች ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም በዕለቱ ድንቅ የነበረው ግብ ጠባቂው አቡሽ አበበ አምክኖባቸዋል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 2 – 1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ወላይታ ድቻዎች የዕለቱን ዋንጫ ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከአቶ አሊሚራህ እጅ በመቀበል የዕለቱ መርሐግብር ፍፃሜ ሆኗል።

እይታ ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች

* በጨዋታው ጎል ያስቆጠረው እና ክህሎቱን ያሳየው የአዳማ ከተማው አማካይ ስምንት ቁጥር ለባሹ ያብስራ አክሊሉ የጨዋታው ኮከብ ነበር፡፡

*በወላይታ ድቻ በኩል ቡድነኑ አሸንፎ እንዲወጣ ያስቻለው አራት ቁጥር ለባሹ አማካይ ምስክር መለሰ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ነበር ያሳየው፡፡

በመጨረሻም

– በቀጣይ በዚህ የዕድሜ እርከን በሚደረገው የኢትዮዽያ 17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ውስጥ ቡድን ያላቋቋሙ እንደ ወልድያ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ፋሲል ከተማ ፣ ድሬደዋ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና እንዲሁም ከከፍተኛ ሊጉ የሚያድጉ ክለቦች የታዳጊዎችን ጠቀሜታ ተገንዝበው ቡድን እንዲያቋቁሙ መልዕክታችንን  እያስተላለፍን በአንፃሩ እንደ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና ደደቢት ያሉ ቡድኖች ደካማ አቋማቸውን አስተካክለው መቅረብ ይገባቸዋል እንላለን ።

– ውድድሩን በበላይነት የሚመራው አካል የአትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዕድሜ ተገቢነት ላይ ዘንድሮ እንደወሰደው መልካም መሻሻል ሁሉ ለጨዋታ አመቺ ሜዳ በማዘጋጀት  ፣ የውድድሮች መቆራረጥን  ፣ የመርሀግብር አወጣጥ ፣ የጨዋታ ቦታ መቀየያየር  ውድድሩ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ያደረገበት መንገድ አነስተኛ በመሆኑ በሚቀጥለው አመት የውድድር ዘመን  በተሻለ ሁኔታ ውድድሩ የሚመራበትን መንገድ ከወዲሁ ሊያጤንበት እንደሚገባ እንጠቁማለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *