በ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ ኩማሲ ላይ የጋና ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው ጨዋታዎች ውስጥ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም እሁድ ለሚደረገው ጨዋታ 22 ተጫዋቾችን ጨምሮ 33 የቡድን አባላትን በመያዝ ሐሙስ ዕለት ወደ ጋና ተጉዟል። ዋሊያዎቹ ኩማሲ ከተማ ከገቡ በኋላ ግን ጥሩ ያልሆነ አቀባበል እንደገጠማቸው ተነግሯል።
የጋና እግርኳስ ማህበር ባለ ሶስት ኮከቡን ኖዳ ሆቴል ለቡድኑ አዘጋጅቶ የጠበቀ ቢሆንም የሆቴሉ ደረጃ ግን በኢትዮጵያ ቡድን አባላት ተቀባይነት አላገኘም ነበር። የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ሆቴሉን ለመቀየር በከተማው አሉ የተባሉትን ጎልደን ቱሊፕ እና ጎልደን ቢን ሆቴሎች ቢያናግሩም በቦታ ጥበት ምክኒያት ሊሳካላቸው አልቻለም ነበር። እንደተሰማው ከሆነም ቡድኑ በመጨረሻ ምሽት 5 ሰዓት አካባቢ የተሻለ ደረጃ አለው ወደተባለው ሮያል ላሜርታ ሆቴል ተዘዋውሯል።
ብሄራዊ ቡድኑ ተይዞለት የነበረው ኖዳ ሆቴል የግብፅ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ሌሎችም ቡድኖች ከዚህ በፊት የተጠቀሙበት በመሆኑ ቅሬታው ግራ የሚያጋባ ነው ቢባልም የኢትዮጵያ ቡድን አባላት በሆቴሉ ክፍሎች ውስጥ ያለው የአየር ማቀዝቀዣ መበላሸት እና ከሆቴሉ እስከ ስታዲየሙ ያለው ርቀት መብዛትን በምክኒያትነት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሆቴል በኩል ከደረሰበት መጉላላት በተጨማሪ ደረጃውን ያልጠበቀ እና ለጨዋታ የማይመች የትምህርት ቤት ሜዳ ላይ ልምምድ ለመስራት እንደተገደደም ተሰምቷል።
በአንፃሩ የጋና እግርኳስ ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት ጆርጅ አፍሪዬ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀረበለትን ኖዳ ሆቴል አልቀበልም ያለው በሆቴሉ ደረጃ ሳይሆን በሌላ ምክኒያት እንደሆነ ገልፀዋል። እንደ ጆርጅ አፍሪዬ ገለፃ ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሆቴል የቀየረበት ምክኒያት ፍርሀት ነው።
“የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በኖዳ ሆቴል አርፎ ከጋና ጋር ባደረገው ጨዋታ 6 – 1 መሸነፉን ስለሚያውቁ ይህ የመሸነፍ መንፈስ እንዳይጋባባቸው በመፍራት ሆቴል እንደቀየሩ እርግጠኛ ነኝ። በአፍሪካ እግርኳስ እንደዚህ ያለ የአጋንንት ፍርሃት የተለመደ ነው፤ ሆቴል መቀየርም መብታቸው ነው፤” ሲሉ ዘና የሚያደርግ አስተያየት ሰጥተዋል።
የጋና እና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ እሁድ ምሽት 12፡30 ላይ በኩማሲው ባባያራ ስፖርትስ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን በዲኤስቲቪ ሱፐርስፖርት 3 ላይ ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ይሆናል።