ካሜሩን 2019 ፡ ሴራሊዮን ማጣሪያውን በድል ጀምራለች

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ስድስት ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደለችው ሴራሊዮን ኬንያን ፍሪታውን ላይ አስተናግዳ 2-1 ማሸነፍ ችላለች፡፡ በሲያካ ስቲቨንስ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኬንያ በመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ በማጣቷ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ግዜ በ10 ተጫዋች ለመጨረስ ተገዳለች፡፡

በጨዋታው መጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ በኬንያ የግብ ክልል ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ የሃራምቤ ከዋክብቶቹ አሰልጣኝ ስታንሊ ኦኮምቢ ይዘዉት የገቡት አሰላለፍ ለመከላከል የፈለጉ አስምስሏቸዋል፡፡ ኬንያ በጨዋታው ቀዳሚ መሆን የምትችልበትን እድል ነፃ የነበረው መስኡድ ጁማ ከአማካዩ ኤሪክ ጆና በድንቅ ሁኔታ የተመቻቸ ኳስ ቢያገኝም ወርቃማውን እድል ሳይጠቀምበት የሊዮን ከዋክብቶቹ ግብ ጠባቂ ዞምቦ ሞሪስ አምክኖበታል፡፡ ሴራሊዮን በ21ኛው ደቂቃ ካይ ካማራ ያሸገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጊብሪላ ዎቢ በቦኒፌስ ኦሉች መረብ ላይ አሳርፏል፡፡

ኬንያ 1-0 መመራት ከጀመረችበት ቅፅበት አንስቶ በጆና፣ ቪክቶር ዋኒያማ እና ሚካኤል ኦሉንጋ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችላለች፡፡ ነገር ግን ተከላካዩ ብራያን ማንዴላ ካማራ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በ42ኛው ደቂቃ ከሜዳ ተወግዷል፡፡

ሁለተኛው 45 በዝናብ ታጅቦ ሲካሄድ ሃሳ ሚላ የሴራሊዮንን መሪነት ማጠናከር የሚችልበትን አጋጣሚ ተንሸራቶ በመውደቁ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ሚላ በ63ኛ ደቂቃ የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡ ለኬንያ ተከላካዮች የራስ ምታት የነበረው እና የእግርኳስ ህይወቱን በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ኬይ ካማራ ላይ ኤሪክ ኦማ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ኡማሩ ባንጉራ በ68ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ኦሉንጋ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ በግሩም ሁኔታ ቅጣት ምት ቢያስቆጥርም ኬንያ ከ12 ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በኃላ እጇን ሰጥታለች፡፡

ሴራሊዮን ምድብ 6 መምራት ስትጀምር የምድቡ ሌላ ጨዋታ ነገ ኩማሲ ላይ በጋና እና ኢትዮጵያ መካከል ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *