ካሜሩን 2019፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ጊኒ እና ሞዛምቢክ ያልተጠበቀ  ድል አስመዝግበዋል

ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቅዳሜ በበርካታ የአፍሪካ ከተሞች ቀጥለዋል፡፡ ከአርብ ጀምሮ ያልተጠበቁ ውጤቶች መመዝገባቸውን በቀጠሉበት የማጣሪያ ጨዋታዎች ደቡብ አፍሪካ፣ ጊኒ፣ ሞዛምቢክ እና ሞሪታንኒያ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ይዘው ሲመለሱ ማሊ፣ ሴኔጋል፣ የወቅቱ ቻምፒዮኗ ካሜሮን፣ ቡሩንዲ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ማላዊ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳው እና ዲ.ሪ. ኮንጎ በሜዳቸው ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ምድብ 1

ዳካር ላይ ኤኳቶሪያል ጊኒን ያስተናገደችው ሴኔጋል በቀላሉ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 አሸንፋለች፡፡ የቴራንጋ አናብስቶቹ በሙሳ ሶ የግንባር ኳስ አማካኝነት በአንደኛው ደቂቃ ግብ መምራት ሲችሉ ሶ ሁለተኛውን ግብ በ73ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ኢድሪሳ ጋና ጉዬ ሶስተኛውን የማሸነፊያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ምድቡን ሴኔጋል እና ሱዳንን ከሜዳዋ ውጪ አርብ ያሸነፈችው ማዳጋስካር በእኩል ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመሩታል፡፡

ምድብ 2

ካሜሩን እና ማላዊ ማጣሪያውን በድል ከፍተዋል፡፡ ካሜሮን ሞሮኮን እንዲሁም ማላዊ ኮሞሮስን በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ካሜሮን በቀጥታ በውድድሩ ላይ የምትሳተፍ ቢሆንም በምድብ የምታደርጋቸው ጨዋታዎች እና ነጥቦች የሚያዙ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያዊያኒ ዳኞች ባምላክ ተሰማ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ ሃይለራጉኤል ወልዳይ እና ዘካሪያስ ግርማ በመሩት የያውንዴው ጨዋታ የማይበገሩት አናብስቶቹ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ግብ ታግዘው ሞሮኮን ድል አድርገዋል፡፡ ቪንሶ አቡበከር በ29ኛው ደቂቃ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ካሜሩንን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ የአትላስ አንበሶቹ በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነት ግብ ለማግኘት በርካታ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ጨዋታው 1-0 ተጠናቅቋል፡፡

ሊሎንጉዌ ላይ ማላዊ ኮሞሮስን 1-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ የማላዊን የድል ግብ ጌራልድ ፒሪ በ32ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ምድቡን ካሜሮን እና ማላዊ ይመሩታል፡፡

ምድብ 3

ቡሩንዲ ደቡብ ሱዳንን እንዲሁም ማሊ ጋቦንን ያሸነፉበት ውጤት በዚህ ምድብ በተደረጉ ጨዋታዎች ተመዝግበዋል፡፡ ቡጁምቡራ ላይ ቡሩንዲ ደቡብ ሱዳንን 3-0 ረታለች፡፡ ሶስቱም ግቦች በመጀመሪያው አጋማሽ ተቆጥረዋል፡፡ ሴድሪክ አሚሴ በ15ኛው ደቂቃ ቡሩንዲን መሪ ሲያደርግ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ጋኤል ዱሃሂንዳቪ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ልማደኛው ፊንስተን አብዱልራዛክ ሶስተኛውን ግብ ጁማ ጄናሮ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ባማኮ ላይ ማሊ ከመመራት ተነስታ ጋቦንን 2-1 ረታለች፡፡ ጋቦን ለጨዋታው ወሳኙን አጥቂ ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግን ይዞ ሳትቀርብ ቀርታለች፡፡ የመስመር ተጫዋቹ ዴኒስ ቦአንጋ በሶስተኛው ደቂቃ ጋቦንን ቀዳሚ ሲያደርግ ካሊፋ ኩሊባሊ እና የቪስ ቢሶማ በሁለተኛው 45 አከታትለው ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ማሊን አሸናፊ አድርገዋል፡፡ ምድቡን ቡሩንዲ ትመራዋለች፡፡

ምድብ 5

ያልተጠበቀ ውጤት በተመዘገበበት ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ከሜዳዋ ውጪ ናይጄሪያን 2-0 አሸንፋለች፡፡ ናይጄሪያ ለሁለት ሳምንታት በፈረንሳይ ጠንከራ ዝግጅት ብታደርግም ስትዋርት ባክተርን አሰልጣኝ አድርጋ በሾመችው ደቡብ አፍሪካ በሜዳዋ እና ደጋፊዋ ፊት ሽንፈትን ቀምሳለች፡፡ ኡዮ ላይ በተካሄደው የሁለቱ ሃገራት ጨዋታ ቴኮሎ ራንቴ በግንባሩ በመግጨት ባፋና ባፋናን በ54ኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ በ80ኛው ደቂቃ ፐርሲ ታኦ ኪገን ዶሊ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ሁለተኛዋን ግብ አክሏል፡፡ ታኦ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባበት ቅፅበት በመልሶ ማጥቃትን ያገኘውን እድል ግብ ጠባዊውን ዳንኤል አኪፒን ጭምር በማለፍ ነው ግብ ሊያስቆጥር የቻለው፡፡ ሊቢያ ምድቡን ደቡብ አፍሪካን በግብ ክፍያ በልጣ ትመራለች፡፡

 

ምድብ 6

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ሴራሊዮን ኬንያን ፍሪታውን ላይ 2-1 ረታለች፡፡ ጊብሪላ ዎቢ እና ኡማሩ ባንጉራ ባስቆጠሩት ግቦች የሊዮኔ ከዋክብቶቹ ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲያሳኩ አስችለዋል፡፡ የሃራምቤ ከዋክብቶቹ ከመሸነፍ ያዳነችውን ግብ ሚካኤል ኦሉንጋ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሴራሊዮን ምድቡን በሶስት ነጥብ ስትመራ ዛሬ 12፡30 ላይ ጋና ኢትዮጵያን ኩማሲ ላይ ታስተናግዳለች፡፡ ጨዋታው በሱፐርስፖርት 3 እና ቤን ስፖርት 2 ኤችዲ ቻናሎች የቀጥታ ስርጭት ያገኛል፡፡

 

ምድብ 7

በኮንጎ ደርቢ ኪንሻሳ ላይ የተጋናኙት ሁለቱ ኮንጎዎች በዲ.ሪ. ኮንጎ 3-1 አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቅቋል፡፡ ሴድሪክ ባካምቡ ዲ.ሪ. ኮንጎን በ20ኛው ደቂቃ መሪ ሲያደርግ ቲዮቪ ቢፎማ የመጀመሪያው 45 ሊጠናቀቅ ሲል ኮንጎ ብራዛቪልን አቻ አድርጓል፡፡ ባካምቡ በ56ኛው ደቂቃ ኮንጎ ኪንሻሳን ዳግም መሪ ሲያደርግ ቻንስል ምቤምባ በ90ኛው ደቂቃ የዲ.ሪ. ኮንጎን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ዲ.ሪ. ኮንጎ ስትመራ ዚምባቡዌ ከላይቤሪ ዛሬ ሃራሬ ላይ ይጫወታሉ፡፡

 

ምደብ 8

ባአኪ ላይ ጊኒ ሃይልነቷ እያከተመ የመጣውን ኮትዲቯርን 3-2 ባልተጠበቀ መልኩ ማሸነፍ ችላለች፡፡ ባለሜዳዋ ኮትዲቯር ሁለት ግዜ ብትመራም ጊኒ ከኃላ ተነስታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ችላለች፡፡ ሰይዱ ዶምቢያ ሁለት ግዜ ዝሆኖቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ቢያስቆጥርም የሰይዶ ዲያሎ፣ ፍራንሶአ ካማና እና በጀርመን ቡንደስሊጋ ድንቅ የውድድር አመት ያሳለፈው ነቢ ኬይታ ያስቆጠሯቸውን ሶስት ግቦች አሰልጣኝ ላፒ ባንጉራንን እና ልጆቻቸውን ለድል አብቅተዋል፡፡ ቤልጄማዊው የኮትዲቯር አሰልጣኝ ማርክ ዊልሞት በዝሆኖቹ ቤት ከወዲሁ ውጤቶችን ማግኘት እየተሳነው ይገኛል፡፡ ባደረጋቸውን ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎችም ተሸንፏል፡፡ ምድቡን ጊኒ ስትመራ ዛሬ ባንግዊ ላይ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሩዋንዳን ታስተናግዳለች፡፡

ምድብ 9

ቡርኪናፋሶ አንጎላን 3-1 ስትረታ ሞሪታንያ ከሜዳዋ ውጪ ቦትስዋናን አሸንፋለች፡፡ ፍራንሲስታውን ላይ በተካሄደ ጨዋታ ሞሪታንያ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠረችው ግብ ታግዞ ቦትስዋናን 1-0 አሸንፋለች፡፡ ሃሩና አቡ ድምባ ሴ በረጅሙ ከራሱ የግብ ክልል የላከውን ኳስ በአግባቡ ማውጣት ያልቻለውን የቦትስዋናውን ተከላካይ ቀምቶ አጥቂው መሃመድ አብዱላሂ ሱዳኒ ስህተት ሳይሰራ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡

ዋጋዱጉ ላይ ቡርኪናፋሶ አንጎላን 3-1 ረታለች፡፡ አንጋፋውን አጥቂ አሪስቲድ ባንሴ በ21ኛው ደቂቃ ቡርኪናን መሪ ሲያደርግ ከሁለት ደቂቃ በኃላ ግሌሰን ዳላ አንጎላን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ ባንሴ በፍፁም ቅጣት ምት ቡርኪናን በ42ኛው ደቂቃ ዳግም መሪ ሲያደርግ በርትራንድ ትራኦሬ በ79ኛው ደቂቃ ጨዋታውን የጨረሰበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቡርኪናፋሶ ትመራለች፡፡

 

ምድብ 10

ኒያሚ ላይ ኒጀር ከስዋዚላንድ ያለግብ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡ ባለሜዳዋ ኒጀር በጨዋታው በርካታ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ብትችልም ሳትጠቀምባቸው ቀርታለች፡፡ ዛሬ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ቱኒዝ ላይ ቱኒዚያ ከግብፅ በተጠባዊ ጨዋታ ይፋጠጣሉ፡፡

 

ምድብ 11

ያልተጠበቀ ውጤት በመዘገበበት በዚሁ ምድብ ሞዛምቢክ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ታግዛ ዛምቢያን ስትረታ ጊኒ ቢሳው ናሚቢያን ማሸነፍ ችላለች፡፡ ንዶላ ላይ ሞዛምቢክ ዛምቢያን 1-0 በመርታት አስገራሚ ውጤትን ይዞ ተመልሳለች፡፡ ቺፖሎፖሎዎቹ የጨዋታም ይሁን የሙከራ የበላይነት ቢኖራቸውም ያገኙትን እድሎች አለመጠቀማቸው የኃላ ኃላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ የፊት አጥቂው ራቲፎ የሞዛምቢክን የድል ግብ በ90ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ የሞዛምቢኩ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ አቤል ሃቪየር ዛምቢያን እንደሚያሸንፉ ከጨዋታውን በፊት የተናገሩትን ቋል አክብረዋል፡፡

ቢሳው ላይ ጊኒ ቢሳው ናሚቢያን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏለች፡፡ የድል ግቡን ኢዲ ጎሜዝ በ23ኛው ደቂቃ አስመዝግቧል፡፡ ምድቡን ሞዛምቢክ እና ጊኒ ቢሳው ይመሩታል፡፡

 

ምድብ 12

ሌሶቶ ዳሬ ሰላም ላይ ከታንዛኒያ ጋር ነጥብ ተጋርታ ወጥታለች፡፡ አስፈሪ የፊት መስመርን ይዞ ወደ ሜዳ የገባችው ታንዛኒያ አሁንም በወሳኝ ጨዋታዎች ድል ሊቀናት አልቻለም፡፡ ምባዋና አሊ ሳማታ በ28ኛው ደቂቃ ታንዛኒያን መሪ ሲያደርግ ታፔሎ ቴል ሌሶቶ ወሳኝ ነጥብ ይዞ የወጣችበትን የአቻነት ግብ በ35ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡

በዚሁ ምድብ ሊካሄድ የነበረው የኬፕ ቨርድ እና ዩጋንዳ ጨዋታ የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከዳካር ወደ ፕራያ የሚያደርጉት የአየር ጉዞ በመዘግየቱ ለዛሬ ተላልፏል፡፡

የአርብ ውጤት

ሱዳን 1-3 ማዳጋስካር

ሊቢያ 5-1 ሲሸልስ

 

የቅዳሜ ጨዋታዎች

ማላዊ 1-0 ኮሞሮስ

ብሩንዲ 3-0 ደቡብ ሱዳን

ካሜሩን 1-0 ሞሮኮ

ዛምቢያ 0-1 ሞዛምቢክ

ቦትስዋና 0-1 ሞሪታንያ

ጊኒ ቢሳው 1-0 ናሚቢያ

ኒጀር 0-0 ስዋዚላንድ

ሴራሊዮን 2-1 ኬንያ

ናይጄሪያ 0-2 ደቡብ አፍሪካ

ኮትዲቯር 2-3 ጊኒ

ቡርኪናፋሶ 3-1 አንጎላ

ዲ.ሪ. ኮንጎ 3-1 ኮንጎ ሪፐብሊክ

ማሊ 2-1 ጋቦን

ታንዛኒያ 1-1 ሌሶቶ

ሴኔጋል 3-0 ኤኳቶሪያል ጊኒ

 

የእሁድ ጨዋታዎች

15፡00 – ዚምባቡዌ ከ ላይቤሪያ (ናሽናል ስፖርትስ ስታዲየም)

15፡00 – የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከ ሩዋንዳ (ስታደ ባርተለሚ ቦጋንዳ)

15፡30 – ጋና ከ ኢትዮጵያ (ባባ ያራ ስፖርትስ ስታዲየም) (በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር 12፡30)

16፡00 – ቤኒን ከጋምቢያ (ስታደ ደ አሚቴ ደ ኮኦኑ)

16፡30 – ኬፕ ቨርድ ከ ዩጋንዳ (ፕራያ ስታዲየም)

22፡00 – አልጄሪያ ከ ቶጎ (ስታደ ሙስጠፋ ቻካር)

23፡00 – ቱኒዚያ ከ ግብፅ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)

Leave a Reply