አትዮዽያውያን ዳኞች ከፊፋ በመጡ ኤምኤ ኤሊት ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቀዋል፡፡ ከግንቦት 22 ጀምሮ ላለፉት 10 ቀናት ሲሰጥ የሰነበተው የዳኝነት ኮርስ ስልጠና ትላንት በካፒታል ሆቴል ሲጠናቀቅ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እና የዳኞች ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ተገኝተዋል፡፡
ሰባት ኢንተርናሸናል ዋና ዳኞች ፣ ሰባት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች እንዲሁም አራት ኢንተርናሽናል ሴት ዋና ዳኞች እና ረዳት ዳኞች ፣ አስር ፌደራል ዋና እና ረዳት ዳኞች እና ኢንስትራክተሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ 41 ሰልጣኞች ተሳትፈውበታል።
አዲሱ የፊፋ ህግ ከተሻሻለ በኋላ ኢትዮዽያውያን ዳኞች ስልጠናውን ሲያገኙ የመጀመርያቸው ሲሆን የማላዊ እና የዚንንባብዌ ዜግነት ባላቸው ባለሙያዎች የተሰጠው ስልጠና በዋናነት በአካል ብቃት እና የተግባር ትምህርት ላይ ያተኮረ ነበር።
ሰልጣኞች በስልጠናው እጅግ ጠቃሚ የሆነ እውቀት እንዳገኙበት ተናግረው በተለይ በ2017 የወጡ አዳዲስ ህጎችን የማወቅ እድል እንዳገኙና በተጨማሪ ከሰኔ ወር ጀምሮ በኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የሚተገበረው አዳዲስ ህጎችን በሚገባ እንዲያውቁ እንደረዳቸው አያይዘው ተናግረዋል ።
በስልጠናው ማብቂያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ጁነይዲ ባሻ በዳኝነት በኩል መሰራት ያለበት ስራ ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጋር በመሆን ወደ ፊትም ተመሳሳይ ስልጠናዎችን ዳኞቻችን እንዲያገኙ ያልተቋረጠ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀው የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። በተጨማሪም አቶ ጁነይዲ ዳኞቻችንም ከዲሲፒሊን ጀምሮ እስከ ዳኝነት አፈፃፀም ጠንክረው እንዲሰሩ መልክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ከዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ባገኘነው መረጃ መሰረት በሚቀጥለው የውድድር አመት አሁን ከተገኘው ስልጠና ልምድ በመውሰድ ወጣት ዳኞች እያሳዩት ካለው እድገት አኳያ ለወጣት ዳኞች እድሉን ለመስጠት እንደታሰበና ኢትዮዽያን የሚወክሉ ኢንተርናሽናል ዳኞች ቁጥር ለመጨመር ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ ታውቋል ።
ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በአለም አቀፍ መድረክም ሆነ በአፍሪካ ሀገራት በሚደረጉ የሀገራትና የክለቦች ውድድሮች ላይ ኢትዮዽያውያን በኢንተርናሽናል ዳኞቻችንን እየተመለከትን እንደሆነ ይታወቃል ።