ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ለ20 አመት በታች ጥሎ ማለፍ ፍጻሜ አለፉ

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል፡፡

የ2009 የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥሞ 2-0 አሸንፏል፡፡ ተመጣጣኝ ፍክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ለመንቀሳቀስ ቢምክሩም ወደ ግብ በመድረስ ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ፡፡ በተለይም በጨዋታው ድንቅ የነበረው ቸርነት አውሽ እና ቴዎድሮስ መሀመድ አጋጣሚዎችን በመፍጠር ረገድ ጥሩ ነበሩ፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ያሬድ መሀመድ ከፀጋአብ ጋር ጥሩ ቅብብል ካደረጉ በኃላ የተገኘውን ኳስ ቸርነት አውሽ ክለቡን ቀዳሚ አድርጎ የመጀመሪያው አጋማሽ በሀዋሳ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች አንድ ኢላማዋን የጠበቀች ኳስ በተስፋዬ በቀለ ካደረጉት ውጭ ተጨማሪ ሙከራ አላደረጉም፡፡ በመከላከል ተጠምደውም ታይተዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ በርካታ አጋጣሚን መፍጠሩን በመቀጠል በ59ኛው ደቂቃ ያሬድ መሀመድ ከቀኝ መስመር በግምት ከ35 ሜትር ርቀት የመታት አስደናቂ ኳስ መረብ ላይ አርፋ ሀዋሳ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መከላከያ ከ አዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አዳማ ከተማዎች ከዕረፍት በፊት ኢሳ ንጉሴ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ ሆነው ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ግብ አስቆጥረው አቻ ቢሆኑም አዲስ ግርማ አዳማ ከተማን ለፍፃሜ ያደረሰች ወሳኝ ግብ አስቆጥሮ  ጨዋታው በአዳማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታ የፊታችን ዕሁድ በ9፡00 በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታድየም ሲደረግ ሊጉን ቻምፒዮን ሀዋሳ ለሁለትዮሽ ድል ፣ ሊጉን በ4ኝነት ያጠናቀቀው አዳማ ለአመቱ የመጀመርያ ዋንጫ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡

በጨዋታው ድንቅ የነበረው የሀዋሳ ከተማው ቸርነት አውሽ

1 Comment

  1. ቸርዬ ምርጥ ልጅ የትም ትደርሳለህ ተሜ ዋንጫው ን ለሁለተኛ ጊዜ ታነሳዋለህ ሶከሮች ለወጣቶች እግር ኳስ ትልቅ ስራ እየሰራቹ ነው በርቱ ዋው

Leave a Reply