የጨዋታ ሪፖርት | ዋልያዎቹ በከባድ ሽንፈት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድራቸውን ጀምረዋል

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ስድስት የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ኩማሲ ላይ ከጋና አቻው ጋር አድርጎ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፏል።

ለ4-2-3-1 በቀረበ ቅርፅ ጨዋታውን የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ 4-4-2/4-4-1-1 የተጨዋቾች አደራደር ወደ ሜዳ የገባውን እና የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ለመጠቀም በሚረዱ የመስመር አማካዮች የተዋቀረውን የጋና ብሔራዊ ቡድን የማጥቃት አጨዋወት ለመቋቋም እጅግ የተቸገረበት ረጅም 90 ደቂቃዎች በኩማሲ አሳልፏል።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሙሉ ለሙሉ ከኳስ ጀርባ በመሆን እና በመከላከል የጀመሩት ዋልያዎቹ ኳስ በሚያገኙበት አጋጣሚ ወደፊት ለመሄድ ያደርጉት የነበረው ጥረት በተወሰነ መልኩ ተስፋ የሚሰጥ አይነት ነበር ። ሆኖም የተጋጣሚያቸውን ክፍተት ለመረዳት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ የፈጀባቸው ጋናዎች የማጥቃት መስመራቸውን በግራ መስመር አማካዩ ቶማስ አግዬፖንግ በኩል ባጋደለ መልኩ በማድረግ በርካታ የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር አልዘገዩም ።

አስረኛው ደቂቃ ላይ አግዬፖንግ ስዩም ተስፋዬን በሩጫ በመቅደም ያሻማውን ኳስ አሳማዎ ጂያን በግንባሩ ሲገጭ ኳሷ አቤልን ካለፈች በኋላ ሙጂብ ቃሲም በደረቱ ከመስመር ላይ ለማውጣት ሞክሮ ሳይሳካለት በራሱ ላይ ግብ አስቆጥሯል። ይህ ጎል ሲቆጠር አሳማዎ ጂያን እና ራፋዬል ዱዋሜና እርስ በእርሳቸው ሲሻሙ አንድም ተከላካይ አብሯቸው አልነበረም። ይህ አጋጣሚም የኢትዮጵያዊያኑን የመከላከል ችግር ፍንትው አርጎ ያሳየ ነበር።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ከመጀመሪያው በባሰ መልኩ መረጋጋት ተስኗቸው ታይቷል። ጋናዎችም ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ተጨማሪ አራት ደቂቃዎች ብቻ ነበር ያስፈለጓቸው። በዚህም 14ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ከግራ መስመር በተሻገረ ኳስ መነሻነት የመሀል ተከላካዩ ጆን ቦዬ የአጥቂ በሚመስል አጨራረስ ከአራት ተከላካዮች መሀል ሆኖ ወደግቡ በመዞር  ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል ። እንደመጀመሪያው ሁሉ ሁለተኛውም ጎል የተከላካይ መስመሩ አለመናበብ ውጤት ነበር ማለት ይቻላል።

በ17ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ለጌታነህ አሻምቶለት ጌታነህ ሳይደርስበት ከቀረው አጋጣሚ ውጪ በመጀመሪያው አጋማሽ  የተሻለ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ዋልያዎቹ አልፎ አልፎ ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በጋንዉያኑ ጫና ምክንያት ስኬታማ ሊሆን አልቻለም ። የቡድኑ ተሰላፊዎች በራሳቸው ሜዳ ላይ በመከላከል ስራ ተጠምደው በቁጥርም በዝተው ይታዩ እንጂ የጋና ተጨዋቾች በሁለቱ መስመሮችም ሆነ በሜዳው ቁመት መሀል ለመሀል ዕድሎችን ለመፍጠር አልተቸገሩም ። 40ኛው ደቂቃ ላይም የጋናው አማካይ ኢቤኔዘር ኦፎሪ ጋቶች ፓኖምን አታሎ በማለፍ ከረጅም ርቀት በግራ እግሩ ግሩም ጎል በማስቆጠር የጋናን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። ጋናዎች ካገኟቸው በርካታ የቆሙ ኳሶች አንፃር የግብ መጠኑ ከዚህም በላይ ከፍ ሊል የሚችልበት ዕድል የነበረ ቢሆንም የኦፎሪ ጎል የመጀመሪያው ግማሽ የመጨረሻ ግብ ነበረች።

ከዕረፍት መልስ ባለሜዳዎቹ እና ጨዋታውን የመሩት አልቢትሮች ወደሜዳ ከገቡ ከደቂቃዎች በሁዋላ ከመልበሻ ቤት የወጡት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የተጨዋች ቅያሪያቸውን ሙሉአለም መስፍንን በሳላዲን ሰይድ በመቀየር አድርገዋል ። ሆኖም ጨዋታው እንደተጀመረ 47ኛው ደቂቃ ላይ ጋናዎች የፈጠሩትን የግብ ዕድል አቤል ማሞ ካዳነ በኋላ በግብ አቅራቢያ የነበሩት ተከላካዮች ኳስን በአግባቡ ማራቅ ተስኗቸው   የፊት አጥቂው ራፋዬል ዱዋሜና አራተኛውን ግብ ሊያስቆጥር ችሏል። ዱዋሜና 60ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሜ ከግራ መስመር የተነሳውን እና አቤል የተፋውን ኳስ አግኝቶ ከተመሳሳይ ቦታ ላይ የጨዋታውን የመጨረሻ ጎልም ማከል ችሏል ። ይህ ጎል ሲቆጠር ጉዳት ያስተናገደው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞም ከግቡ መቆጠር በኋላ በጀማል ጣሰው ተቀይሮ ወጥቷል ። በእነዚህ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በ55ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም ከሽመልስ ጋር በመቀባበል ከረጅም ርቀት ሞክሮ ወደውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻለም።

በቀሪዎቹ 30 ደቂቃዎች በተለይም በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያው በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከረ ሲሆን በጋቶች ፓኖም ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ ሳላዲን ሰይድ እና ኡመድ ኡኩሪ አማካይነት የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። ሆኖም ሙከራዎቹ ከጋና የግብ ክልል እጅግ ርቀው የሚደረጉ በመሆናቸው እና የጥቋቁር ኮከቦቹን የተከላካይ መስመር አልፈው ከግብ ጠባቂው ጋር የሚያገናኙ የመጨረሻ ኳሶች መፈጠር አለመቻላቸው ቡድኑ ግብ እንዳያገኝ ምክንያት ሆነውበታል።  በተቃራኒው ጋናዎች በርካታ ያለቀላቸው ዕድሎችን ቢፈጥሩም የግብ መጠኑን ግን ከ አምስት ከፍ ሳያደርጉት ጨዋታው ተጠናቋል።

በውጤቱም ጋና ምድቡን መምራት ስትጀምር ትላንት ኬንያን የረታችው ሴራሊዮን በግብ ልዩነት አንሳ በሁለተኛነት ትከተላለች። ተሸናፊዎቹ ኬንያና ኢትዮጵያም በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በካሜሩኑ የ2019 የአህጉሪቱ ዋንጫ ላይ ለመካፈል የሚደረገው ይህ ውድድር ከስምንት ወራት በኋላ ሲቀጥልም ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን እንዲሁም ኬንያ ጋናን በሜዳቸው የሚያስተናግዱ ይሆናል።

5 Comments

    1. How did you use the amharic fornt here? Couldnt see any features I can use.

  1. Woy agger, woy agger, woy agger enat……!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!
    By battle of Adawa our hero father had defeated the invading war of Italia before several years. But now our football team has been defeated shamefully on the battle of Kumasi by black stars. I heard as some foot ball fans of our team have predicated as Ethiopia would won the game with 2-0 score. I replied to them as that predication is somewhat joking on football. Because we could not win even Ugandan football team at our home on the friendship game held here at Addis. So I would like to encourage the coach to work hard just by forgetting about the passed game and to look forward with additional strategies.

  2. Mekelakele bichawun kemeshenefe ayadinim ,these is national team,not addama fc

Leave a Reply