ጥሎ ማለፍ | ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሩብ ፍጻሜ ተሸጋግረዋል

የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የ2ኛ ዙር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎችን አስተናግዶ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀሉበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡

08:30 ላይ በወላይታ ድቻ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ እስካሁን ከተደረጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የተሻለ ፉክክር አስተናግዶ በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ተመጣጣኝ በነበረው በመጀመርያው አጋማሸ በሁለቱን በኩል ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና የግብ ሙከራዎች የተስተዋሉ ቢሆንም ግብ ሳይስተናገድ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ የመጀመርያ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ድቻዎች ዮሴፍ ድንገቱ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ጠርዝ በመምታት ባስቆጠራት ግብ የጨዋታው አሸናፊ የሚሆኑበትን ጎል ማግኘት ችለዋል፡፡ ከግቡ በኋላ አርባምንጮች ተጭነው በመጫወት የአቻነት ጎል ለማግኘት ያደጓቸው ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ በተለይ በቀኝ መስመር ካመዘነው የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚሻገሩት ደካማ  ተሻጋሪ ኳሶችን የድቻ ተከላካዮች በቀላሉ ሲቆጣጠሯቸው ተስተውሏል፡፡

ቀጥሎ የተደረገው ጨዋታ አትዮጵያ ቡናን ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ከዚህ አለም በሞት የተለየው አሰግድ ተስፋዬን ለማሰብ በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር የተዘጋጀ ባነር ይዘው በመግባትና በህሊና ጸሎት በተጀመረው ጨዋታ 10ኛው ደቂቃ ላይ አሰግድ ፣ 12ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት ከዚህ አለም በሞት የተለየው የኢትዮጵያ ቡና አስጨፋሪ ይድነቃቸው በጭብጨባ ታስበዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ቀስ በቀስ ጨዋታው እየተቀዛቀዘ በመሀል ሜዳ ላይ ወዳመዘነ እንቅስቃሴ ተሸጋግሯል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩት ቡናዎች ያልተሳኩ የማጥቃት ሙከራዎች ሲያደርጉ አልፎ አልፎ ወደ ቡና የግብ ክልል ሲጠጉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ተሳክቶላቸዋል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ ፍፁም ገብረማርያም በቡና የግብ ክልል ግራ አቅጣጫ ተከላካዮችን ሚዛነ በማሳት በግሩም አጨራረስ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ሲያደርግ በ89ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በረከት ተሰማ ወደ ግብነት ቀይሮ የኤሌክትሪክን መሪነት አስተማማኝ አድርጎታል፡፡

የቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ ከአሰልጣኝ እድሉ ደረጀ ጋር የፈጠሩት አለመግባባት እንዲሁም የቡና ደጋፊዎች በቡድናቸው እና አሰልጣኝ ላይ የገለፁት ብስጭት የጨዋታው ክስተቶች ነበሩ፡፡

በጥሎ ማለፉ 2ኛ ዙር መደረግ ከነበረባቸው 8 ጨዋታዎች 6 ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መከላከያ ፣ ወልድያ ፣ ጅማ አባ ቡና ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፉ ቡድኖች ናቸው፡፡ ሰኔ 11 አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ ፤ ሰኔ 14 ሲዳማ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታም ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉ ቀሪዎቹ ሁለት ቡድኖች የሚለዩ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *