ረጅም ጊዜያት የፈጀው የዋልያዎቹ ረዳት አሰልጣኝነት ሹመት መቋጫ አግኝቷል፡፡ የቀድሞው የፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮን ውበቱ አባተ የፖርቱጋላዊው ማርኖ ባሬቶ ምክትል ሁነው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ወስኗል፡፡
የቅጥሩ ዝርዝር በይፋ ያልተገለፀ ሲሆን በሱዳኑ አህሊ ሼንዲ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው እየሰሩ የሚገኙት ውበቱ ከዋናው አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ጋር በዚህ ሳምንት ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በይፋ የብሄራዊ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከአዲሱ የኢትዮጵውያን ሚሌንየም ወዲህ በእግርኳሳችን ላይ ከታዩት ምርጥ አሰልጣኞች አንዱ የሆኑት አሰልጣኝ ውበቱ የአሰልጣኝነት ሪከርዳቸው ጉራማይሌ መልክን ይይዛል፡፡ በ2000 ትንሹን አዳማ ከነማ ይዘው በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ከረዱ በኋላ ወደ ደደቢት ቢያቀኑም ብዙም ሳይቆዩ ተሰናብተዋል፡፡ በ2003 ኢትዮጵያ ቡናን ተረክበው አደገኞቹን ከ13 አመታት ጥበቃ በኋላ የሊግ ዋንጫ እንዲያነሱ ሲያደርጉ በአመቱ ቡድኑ 11ኛ ሆኖ ማጠናቀቁን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተለያይተው ንግድ ባንክን ተረክበዋል፡፡ በንግድ ባንክ ስኬታማ መሆን የተሳናቸው አሰልጣኝ በአመቱ የሱዳኑ አህሊ ሼንዲን መረዳት አሰልጣኝነት ተረክበው ቡድኑ ላሳየው መሻሻል ተጠቃሽ ተደርገው በክለቡ የምስጋና ምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡