ካሜሩን 2019፡ ጋና፣ ዩጋንዳ፣ ቤኒን እና ቱኒዚያ የማጣሪያ ጉዟቸውን በድል ጀምረዋል

ካሜሩን ከሁለት አመታት በኃላ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የምድብ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታዎች እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ 

የሰሜን አፍሪካ ጎረቤታሞቹ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ በተመሳሳይ 1-0 የሆነ ውጤት ተጋጣሞዎቻቸውን ሲያሸንፉ ጋና ኢትዮጵያ ላይ 5 ግቦችን አስቆጥራ ማጣሪያዋን ጀምራለች፡፡ ዩጋንዳ በጥሩ አቋሟ መቀጠል የቻለችበትን ድል ፕራያ ላይ ስታስመዘግብ ቤኒን እና ዚምባቡዌም ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ምድብ 3

ኮትኑ ላይ ጋምቢያን ያስተናገደችው ቤኒን 1-0 አሸንፋለች፡፡ የተበላሹ ቅብብሎች፣ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች እና የተቀዛቀዘ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ሃገራት መገለጫ ነበር፡፡ ከእረፍት መልስ ስቴፈን ሴሴኞ የቤኒን የድል ግብ አስቆጥሮ ወሳኝ ሶስት ነጥብን ለሃገሩ አስገኝቷል፡፡

አዲሱ የአልጄሪያ ስፔናዊ አሰልጣኝ ሉካስ አልካሬዝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዘመቻቸውን በድል ከፍተዋል፡፡ ብሊዳ አልጄሪያ ቶጎን 1-0 ማሸነፍ ችላለች፡፡ የባለሜዳዎቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በታየበት ጨዋታ ሶፊያን ሃኒ የበረሃ ቀበሮዎቹን የድል ግብ በ24ኛው ደቂቃ በቶጎው ግብ ጠባቂ ሳቢሩ ባሳ ጄሪ አናት ላይ በመስደድ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን ቤኒን እና አልጄሪያ ይመሩታል፡፡

ምድብ 6

ኩማሲ ላይ ኢትዮጵያን የገጠመችው ጋና 5-0 አሸንፋለች፡፡ የባለሜዳዎቹ ፍፁም የሆነ የግብ ሙከራ እና የጨዋታ ብልጫ የእንግዶቹ እቅድ የለሽ የጨዋታ አቀራረብ እና የመከላከል ድክመት በታየበት ጨዋታ የጥቋቁር ከዋክብቶቹን ግቦች አሰሞሃ ጃን (ሙጂብ ቃሲም በራሱ ግብ ላይ አስቆጠረ ቢባልም ካፍ ግቡን ለጃን አፅድቋል)፣ ጆን ቦይ፣ ኤቤኔዘር ኦፎሪ እና ራፋኤል ዱዋሜና ከመረብ አዋህዷል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ለብሄራዊ ቡድኑ የተሰለፈው ዱዋሜና ሁለትት ግቦች ከእረፍት መልስ አስገኝቷል፡፡ አሰሞሃ ጃን ለጋና ያስቆጠረውን የግብ መጠን 50 አድርሷል፡፡

ምድቡን ጋና ሴራሊዮንን በግብ ክፍያ በልጣ ስትመራው ኬንያ እና ኢትዮጵያ ያለምንም ነጥብ 3ተኛ እና 4ተኛ ናቸው፡፡

ምድብ 7

ሃራሬ ላይ ዚምባቡዌ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ላይቤሪያን 3-0 አሸንፋለች፡፡ የቀድሞ የካይዘር ቺፍ አጥቂ ኖሌጅ ሙሶና ሃትትሪክ በሰራበት ጨዋታ አሰልጣኝ ኖርማን ማፔዛ ጦረኞቹን ማጣሪያውን በድል እንዲጀምሩ አስችለዋል፡፡ ሙሶና በ24ኛው ደቂቃ ዚምባቡዌን መሪ ሲያደርግ በ50 እና 63ኛው ደቂቃ ያስቆጠራቸው ተጨማሪ ግቦች ሃገሩን ለአሸናፊነት አብቅቷል፡፡ ምድቡን ዚምባቡዌ ስትመራ በግብ ክፍያ የምታንሰው ዲ.ሪ. ኮንጎ ትከተላለች፡፡

ምድብ 8

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባንጉዊ ላይ ሩዋንዳን በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ አሸንፋለች፡፡ ጁኒየር ጎሬር በ48ኛው ደቂቃ ባለሜዳዎቹን መሪ ሲያደርግ ለኤኤስ ቪታ ክለብ የሚጫወተው ቁመተ ለግላጋው አጥቂ ኤርነስት ሱጌራ በ91ኛው ደቂቃ ሩዋንዳን አቻ አድርጓል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ሳሊፍ ኬይታ ያስቆጠራት ግብ በስታዲየም የተገኘውን ተመልካች እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ የአሁኑ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አሰልጣኝ ራውል ሳቮይን አስፈንድቋል፡፡ ምድቡን ጊኒ ስትመራ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሁለተኛ ነች፡፡

ምድብ 10

በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ቱኒዚያ ግብፅን ቱኒዝ ላይ 1-0 አሸንፋለች፡፡ የቀድሞ አሰልጣኟን ነቢል ማሎልን ወደ አሰልጣኝ መንበሩ የመለሱት የካርቴጅ ንስሮቹ ከፈርኦኖቹ ተሽለው በጨዋታው ታይተዋል፡፡ እንደተጠበቀው ጥብቅ መከላከልን የመረጡት የግብፁ አሰልጣን ሄክቶር ኩፐር ማጣሪያውን በሽንፈት ጀምረዋል፡፡ የድል ግቡን የኤስፔራንሱ ኮከብ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ በሁለተኛው አጋማሽ የሱፍ ሳክኒ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ሻሪፍ ኤክራሚ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ምድቡን ቱኒዚያ ትመራለች፡፡

ምድብ 12

ቅዳሜ ሊደረግ ቀነ ቀጠሮ ወጥቶለት የነበረው እና ለእሁድ የተላለፈው የኬፕ ቨርድ እና ዩጋንዳ ጨዋታ በክሬንሶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ ፕራያ ላይ በተደረገው ጨዋታ ኬፕ ቨርድ በመጀመሪያ 45 አጥቅታ ስትጫወት ዩጋንዳ በመከላከሉ ተጠምዳ ቆይታለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ሚልተን ካሬሳ እና ጆኦፍሪ ሴሬንኩማ ቀይረው አስገብተው ውጤታቸውን አሳምረዋል፡፡ የኬሲሲኤው ሴሬንኩማ በ83ኛው ደቂቃ በጥሩ መልኩ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ከመረብ አዋህዶ ዩጋንዳን ለአሸናፊነት አብቅቷል፡፡ ዩጋንዳ ድሉን ተከትሎ ምደቡን መምራት ጀምራለች፡፡

የአርብ ውጤት

ሱዳን 1-3 ማዳጋስካር

ሊቢያ 5-1 ሲሸልስ

የቅዳሜ ውጤቶች

ማላዊ 1-0 ኮሞሮስ

ብሩንዲ 3-0 ደቡብ ሱዳን

ካሜሩን 1-0 ሞሮኮ

ዛምቢያ 0-1 ሞዛምቢክ

ቦትስዋና 0-1 ሞሪታንያ

ጊኒ ቢሳው 1-0 ናሚቢያ

ኒጀር 0-0 ስዋዚላንድ

ሴራሊዮን 2-1 ኬንያ

ናይጄሪያ 0-2 ደቡብ አፍሪካ

ኮትዲቯር 2-3 ጊኒ

ቡርኪናፋሶ 3-1 አንጎላ

ዲ.ሪ. ኮንጎ 3-1 ኮንጎ ሪፐብሊክ

ማሊ 2-1 ጋቦን

ታንዛኒያ 1-1 ሌሶቶ

ሴኔጋል 3-0 ኤኳቶሪያል ጊኒ

የእሁድ ውጤቶች

ዚምባቡዌ 3-0 ላይቤሪያ

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 2-1 ሩዋንዳ

ጋና 5-0 ኢትዮጵያ

ቤኒን 1-0 ጋምቢያ

ኬፕ ቨርድ 0-1 ዩጋንዳ

አልጄሪያ 1-0 ቶጎ

ቱኒዚያ 1-0 ግብፅ

Leave a Reply