የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ቡና አማካይ የሆነው ጋቶች ፓኖም ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ለሙከራ ያመራል፡፡ የተጫዋቹ ወኪል ዴቪድ በሻ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው አማካዩ ማክሰኞ ወደ ሩሲያ አምርቶ እስከእሁድ ድረስ ከአንዚ የመጀመሪያ ቡድን ጋር ልምምድ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡
አንዚ ለጋቶች የሙከራ ጥሪ ካቀረበለት ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን እንደወኪሉ ዴቪድ ገለፃ ከሆነ ያሉትን አማራጮች ካዩ በኃላ ተጫዋቹ ወደ ሩሲያ ሆዶ የሚሞክርበት እድል ተመቻችቷል፡፡ “የአንዚ ባለስልጣናት በጋቶች ብቃት ደስተኛ በመሆናቸው ነው ይህ እድል ሊገጥመን የቻለው፡፡ ማክሰኞ ወደ ሩሲያ አቅንቶ የህክምና ምርመራ ያደርጋል፡፡ እስከእሁድ ድረስም ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ያደርጋል፡፡ በቀጣይ ስላለው የዝውውር ሁኔታ ከእሁድ በኃላ አብረን የምናየው ይሆናል” ያለው ዴቪድ ጋቶች ለአንዚ ከወዲሁ ለመጫወት መስማማቱን የሚገልፁ ዘገባዎች ላይ ሃሳቡን ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
“አሁን ጋቶች እስከሁድ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ነው የሚሰራው፡፡ ከእሁድ በኃላ አንድ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን፡፡” ይላል ዴቪድ
ጋቶች ፓኖም በኢትዮጵያ ቡና የሚያቆየውን የአንድ ዓመት ከ3 ወር የውል ማራዘሚያ የፈረመው ሚያዚያ ላይ ሲሆን የጋቶች አንዚ ዝውውር የሚሳካ ከሆነ ከቡና ጋር መለያየቱ እውን ይሆናል፡፡ አንዚ በዘንድሮው የሩሲያ ፕሪምየር ሊግ ከ16 ቡድኖች ከቻምፒዮኑ ስፓርታክ ሞስኮ 39 ነጥብ አንሶ በ30 ነጥብ 12ተኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል፡፡ ክለቡ በ2011 እ.ኤአ. በሩሲያው ቢሊየኒየር ሱሌማን ኬሪሞቭ ከፍተኛ መዋለ ንዋይን በማፍሰስ ስምጥር ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሎ ነበር፡፡ በኬሪሞቭ ገንዘብ ለክለቡ ከፈረሙት ታዋቂ ተጫዋቾች መካከል ሳሙኤል ኤቶ፣ ሮቤርቶ ካርሎስ፣ ላሲና ትራኦሬ፣ ዩሪ ዚርኮቭ እና ምባረክ ብሶፋ ይጠቀሳሉ፡፡ ከ2013 ወዲህ ኬሪሞቭ በከፍተኛ ሁኔታ የበጀት ቅነሳ ማድረጋቸውን ተከትሎ ክለቡ ውጤቱ አሽቆልቁሏል፡፡ በ2014ም ከሩሲያ ፕሪምየር ሊግ ለመውረድ ተገዶ ነበር፡፡
በ1991 እ.ኤ.አ. የተመሰረተው አንዚ መቀመጫውን በማካቻካላ ከተማ ያደረገ ሲሆን የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን 26400 ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው አንዚ አሬና ያደርጋል፡፡ ሩሲያዊው አሰልጣኝ አሌክሳንደር ግሪጎሪያን ከጥር ወር ጀምሮ ክለቡን እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡