ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ ፉክክር ልብ አንጠልጣይ ሆኗል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞ ተካሂደዋል፡፡ የምድብ ለ ፉክክርም ልብ አንጠልጣይ የሆነበትን ሳምንት አሳልፏል፡፡

ምድብ ሀ

በምድብ ሀ አመዛኝ ጨዋታዎች ወደ ሰኔ 14 የተዘዋወሩ በመናቸው ቀደም ብሎ በወጣላቸው መርሃ ግብር መከናወን የቻሉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነበሩ፡፡

ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙትና ወደ አንደኛ ሊግ መውረዳቸውን ያረጋገጠጡት ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና አራዳ ክፍለ ከተማን ያገናኘው መርሃ ግብር በሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሌላው በዚህ ምድብ የተደረገው ጨዋታ አክሱም ከተማን ከለገጣፎ ለገዳዲ ያገናኘው ጨዋታ ነበር፡፡ ይህ ጨዋታም ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ምድብ ለ

በዚህ ሳምንት ጨዋታዎች መሪዎቹ ሁለት ቡድኖች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ልዩነቱን በማጥበብ የምድቡን ውጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል፡፡

በግብ ልዩነት ምድቡን የሚመራው ጅማ ከተማ ድሬዳዋ ፓሊስን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ጅማ ከተማ በጨዋታው አሸናፊ ሊሆን የሚችልበትን የፍጹም ቅጣት ምት በ70ኛው ደቂቃ ላይ ቢያገኝም ተመስገን ገብረኪዳን መትቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ወደ ሐዋሳ ያቀናው ሀድያ ሆስዕና ከ ደቡብ ፖሊስ ጋር 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ደቡብ ፖሊሶች ሙሉ የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን በተለየም ግብ ለማስቆጠር በርካታ እድሎችን መፍጠርም ችለዋል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕናን በሁለተኛው ዙር የተቀላቀለው እምሻው ካሱ በ15ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምትኩ ጎአ አስቆጥሮ ደቡብ ፖሊስን መሪ ሲያደርግ በ45ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ሁለተኛውን አክሎ በ2-0 መሪነት እረፍት ወጥተዋል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና የደቡብ ፖሊሱ ተከላካይ  ጢሞቲወስ ቢረጋ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን አጨቃጫቂ ፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ አስቆጥሮ ሆሳዕና ወደ ጨወታው እንዲመለስ አስችሎታል፡፡ ሀዲያ ሆሳህና ከክለቡ ጋር ተጉዘው በመጡት ደጋፊዎች ታግዞ እልህ አስጨራሽ ፍክክር በማሳየት በ79ኛው ደቂቃ ላይ እርቅይሁን ተስፋዬ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ሀዲያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስተው አቻ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ የሀዲያ ሆሳዕናው አምበል ሄኖክ አርፍጮ በጢሞቲወስ ቢረጋ ላይ በፈፀመው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ሲወገድ ሀዲያ ሆሳዕና በ87ኛው ደቂቃ ላይ የቀድምው የወላይታ ድቻ አጥቂ ሳምሶን ቆልቻ ግብ አስቆጥሮ በረዳት ዳኛው ሶርሳ ዱጉማ  ከጨዋታ ውጭ ነው ተብሎ በመሻሩ የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች እና የቡድን አባላት ከፍተኛ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ሀድያ ሆሳዕናም ክስ አስይዞ ጨዋታው ሁለት አቻ ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታውም በኋላ የሀድያ ሆሳዕና አመራሮች ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ከክለቡ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ከሚፎካከር ከተማ ዳኛ መመደቡን ገልጸው ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ወልቂጤ ከተማ በሜዳው አርሲ ነገሌን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ ከመሪዎቹ የነበረውን ርቀት ወደ አንድ ነጥብ ማጥበብ ችሏል፡፡ ብስራት ገበየው በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ማብቂያ ላይ ወልቂጤን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ሲያስቆጥር ከዕረፍት መልስ ወንድወስን ሁለተኛውን ግብ አክሏል፡፡ በምድቡ ግርጌ የሚገኘው አርሲ ነገሌ ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ጎል በ76ኛው ደቂቃ አስቆጥረው ጨዋታው በወልቂጤ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጅንካ ላይ በጂንካ ከተማ እና ሀላባ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በተነሳ ግርግር ተቋርጧል፡፡ ሰላማዊ እና መልካም እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በ43ኛው ደቂቃ ጅንካዎች ቀዳሚ የሚደርጋቸውን ጎል በኃይለ ብርሃኔ አስቆጥረው ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት መልስ ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ሀላባዋች የክለባቸው እና የምድቡ ጎል ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዘካርያስ ፍቅሬ በ52ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ሲችሉ በ62ኛው ደቂቃ አብነት ተሾመ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ሀላባን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ የጅንካ ተጫዋቾች ወደ ረዳት እና መሀል ዳኛው በመሄድ ጭቅጨቅ የፈጠሩ ሲሆን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ረብሻ ተፈጥሮ በመሀል ዳኛው ሚካኤል ጣዕመ ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከ62ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው ሳይቀጥል ቀርቷል፡፡ የሀላባ ተጫዋቾችም ከመጫወቻ ሜዳው ከምሽቱ አንድ ሰዓት አከባቢ በልዩ ታጣቂ ሀይል ታጅበው መውጣታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ወደ ድሬዳዋ ያመራው ሻሸመኔ ከተማ በናሽናል ሲሜንት 2-1 ተሸንፎ ተመልሷል፡፡ አብዱልዚዝ ዑመር በ9ኛው ደቂቃ ሻሸመኔ ከተማን መሪ ማድረግ ቢችልም በ43ኛው እና በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ በተቆጠሩ ግቦች ተሸንፎ ከመሪዎቹ የነበረውን ርቀት የሚያጠብበትን ወርቃማ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ዲላ ከተማ ካፋ ቡናን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በ50ኛው ደቂቃ ላይ የኋላሸት ሰለሞን ለዲላ ከተማ ብቸኛውን የአሸናፊነት ግብ አስቆጥሯል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ በ8፡00 ፌደራል ፖሊስ ነቀምት ከተማን አስተናግዶ በመብራቱ ወልዳይ (ሁለት) እና አብድሪ ሕይም ጎሎች 3-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ሲርቅ ነገሌ ቦረና ስልጤ ወራቤን አስተናግዶ 1-0 በሆን ውጤት ተሸንፏል፡፡

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ እጅግ ከፍተኛ ፉክክር እያስተናገደ የሚገኝ ምድብ ሆኗል፡፡ ሁለት ጨዋታ ብቻ በሚቀረው ምድብ መሪዎቹ እና ከግርጌ የሚገኙ ቡድኖች በነጥብ እጅግ ተጠጋግተው እንደመገኘታቸው አወዳዳሪው አካል በዳኛ ምደባ እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል መልእክታችን ነው፡፡

4 Comments

  1. የዳኞች ስህተት በተለይም የመስመር ዳኛና መሀል ዳኛ አለመናበብ ምክኒያት በተመልካቹም ሆነ በተጫዋቹ አላስፈላጊ ግርግሮች እንዲነሱ የሚያደርጉት። የጂንካና ሀላባ ጨዋታ ፍፁም ሰላማዊና ማራኪ ጫወታ። ነበር ነገር ግን ችግሩ የተከሰተው የዳኞች አለመናበብ ዋናው ምክኒያት ነው። ከዘገባው መስተካከል ያለበት ዳኛውን ተጫዋች አልነካውም ነገር ግን ኳስ የሚያመላልስ ህፃን ልጅ ያልተገባ ተግባር ፈፅሟል እንጂ ተመልካች በሙሉ ወደ ሜዳ አልተገባም እንዲረጋጉና ጥሩና ማራኪ ጫዋታ ለማዬት የተመልካቹ ጉጉት ነበር። የሀላባ ተጫዋቾች ላይ ማንም ጉዳት ለማድረስ ያሰበም ያለመም የለም ምክኒያቱም ከ 3 ተጫዋቾች በላይ ከጂንካ የተቀላቀሉ ልጆች ያሉበት ክለብ ከመሆኑም ባሻግር
    ከሀላባ ተጫዋቾች ጋር ተመልካቹ ፍፁም ሠላማዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። የመሸው ጨዋታው ይቀጥል አቀጥል ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ነው።
    ለማንኛውም የዳኞች ስህተት ዋጋ እያስከፈለን ነው ፌደረሽኑ ዳኞች ላይ ትኩረት ያድርግ አንድ ህፃን ባጠፈው ተመልካቹን በሙሉ አይወክልም……

  2. ዳኛ እና አበት የጠፋ ቤት መቼም ጥሩ አይሆንም ሰለዚህ ስትመድቡም ሆና ስትመለምሉም ለአገሬ ለክብሬ ለኩረቴ ለመንነቴ ለኢትዮጵያ እድገት የወደ ፈት ታስፋ በማለት እንጂ ብሄሬ ክልሌ ጓዳኛዬ …ወዘተ በትሉ የተሰጠላችሁን ሀደራ ተወጡ ጥሩ ብያዲግ ተጠቀም አገሩ ነው

  3. በዳኛ አመዳደብ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለእግዚአብሔር ብሎ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እላለሁ።ምክንያቱም በርካታ ችግሮች በዳኞች አማካይነት እየተፈጠረ ነው።በመሆኑም በቀጣይ ጨዋታዎች ብቃትና ሙያቸውን የሚያከብሩ ዳኞችን ለመመደብ በትኩረት መስራት ነው የሚያስፈልገው ብዬ አስባለሁ።

Leave a Reply