የኢትዮጵያ የውሰጥ ሊጎች ወደ መገባደጃቸው እየተቃረቡ ይገኛሉ፡፡ ሁሉንም ሊጎች በአወዳዳሪነት እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይም ስለ ውድድር ዘመኑ ጉዞ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡
የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና ሊግ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ እንደመሆንዎ በአጠቃላይ የዘንድሮ አመት ውድድሮችን እንዴት ያዩታል?
ዘንድሮ የመራናቸው ሊጎች ስድስት ናቸው፡፡ በአብዛኛው ውድድሮች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ ይገኛሉ። ሆኖም ግን ከፍተኛ ሊግ ላይ አንዳንድ ችግሮች ተደጋግመው እየተፈጠሩ ነው። እንዳወዳዳሪ አካል ችግሩ የተፈጠረው የምንለው ለማለፍ እና ላለመውረድ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሚከሰት መሆኑን እንጂ ሌላ አጀንዳ እንደሌለው ነው የምናቀው። እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ በተቻለ መጠን የሄድንባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው። ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በዲሲፒሊን ኮሚቴው አማካኝነት የዲሲፒሊን ጥሰት የተፈፀመበትን ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ ውሳኔ ወስነናል፡፡ ይህ ደግሞ ጠቅሞናል ብለን እናስባለን። በአጠቀላይ ሁሉም ሊጎች በሰላማዊና ጥሩ በሆነ ሁኔታ ከባለፈው አመት በተሻለ መልኩ እየቀጠሉ ይገኛል። በክለቦች መካከል ያለው መከባበር ፣ በተመልካቹም ዘንድ ያለው የድጋፍ አሰጣጥ አመርቂ ሆኖ ነው ያገኘነው።
የዲሲፕሊን ኮሚቴው አስፈላጊውን የቅጣት ውሳኔ ከወሰነ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን የሚሻርበት መንገድ ፌዴሬሽኑ ላይ ጥያቄ እያስነሳ ነው…
ፌዴሬሽኑ ላይ እንዴት ነው ጥያቄ የሚያስነሳው? እኛ ውሳኔዎችን እናስወስናለን፡፡ ለተፈጠሩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ለፍትህ አካላት ለውሳኔ እንዲሰጥበት የምናቀርበው እኛ ነን፡፡ እንዴት ፌዴሬሽኑ ላይ ጥያቄ ይነሳል። እንደሚታወቀው እግር ኳስ የሚሻሻል ነው። በእግር ኳስ የሚሰሩ ስራዎች በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃሉ። እግር ኳስ የህዝብ ነው ክለቦችን ለሟቋቋም በርካታ የሆነ የህዝብ ገንዘብ ፈሶበታል ፤ ብዙ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ እነዚህን ክለቦችን ደግሞ መጠበቅ አለብን። ለምሳሌ አንድ ተጨዋች ብዙ ጊዜ ሲያጠፋ አራት ሺህ ብር እና አራት ጨዋታ ይቀጣል ፤ ይህ ደግሞ የሚጎዳው ተጨዋቹን ሳይሆን ክለቡን ነው። ተጨዋቹ በገንዘብ ቅጣቱ ነው የሚማረው እንጂ የጨዋታ ቅጣቱ ክለቡን ይጎዳል። ክለቡ ከፍተኛ ገንዘብ እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ለተጨዋቹ አውጥቷል፡፡ ተጨዋቹ ሲቀጣ ሳይጫወት ሲቀር ደግሞ ክለቡ ውጤት ያጣል ክለቡ ይጎዳል። እኛ ደግሞ ክለቡ እንዳይጎዳ ስለምንፈልግ ተጨዋቹ እና ክለቡ ይቅርታ ከጠየቁ እንዲሁም ክለቡ በተጨዋቹ ላይ በውስጥ አሰራር አስተዳደራዊ እርምጃ ከወሰደ ይታይና እንደ ሁኔታው ውሳኔው ሊስተካከል ይችላል ወይም ቅጣቱ ሊቀነስ ይችላል ። ይህ ሲባል ፈፅሞ ሁሉንም ይቅርታ እናደርጋለን ማለት አይደለም ፤ ጥፋቱ ይመዘናል፡፡ ለምሳሌ ዳኛን የደበደበ ፣ የሰደበ ፣ ኮሚሽነሮች እና አመራሮችን በተመሳሳይ የተሳደበና አላስፈላጊ ነገር ያደረገ ፈፅሞ ይቅር አንልም፡፡ ምክንያቱም ዳኞች እና የውድድር አመራሮች መከበር አለባቸው፡፡
በሊግ ኮሚቴ ውስጥ ስራዎች በተወሰኑ ሰዎች ተደራረቦ መሰራቱ ስራው ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ነው ሲባል ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ ለዚህ ምላሻችሁ ምንድን ነው ?
የመረጃ ክፍተት ካልሆነ በቀር እያንዳንዱ የሊግ ውድድር በተለያዩ ሰዎች ነው የሚሰራው፡፡ እንዳውም አዲስ ሰው በመቅጠር የሰው ሀይላችንን ጨምረናል፡፡ ለስደስት ሊግ ስድስት ሰው አለ ፤ በዛላይ ደግሞ ሊጉን የሚመራ በአጠቃላይ አቶ ሰለሞን አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፅህፈት ቤት ሰራተኞች አሉ። ስለዚህ የተፈጠረ ክፍተት እና የተጓደለ ነገር የለም። በሰው ማነስ እና በተደራረበ ስራ ምክንያት የተጓደለ ነገር አለ የሚባለው ነገር በእኛ በኩል የለም ነው መልሳችን።
ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ የኮከቦች ምርጫ በአንድ ደረጃውን በጠበቀ ሆቴል ለማድረግ ፌዴሬሽኑን ያነሳሳው ምክንያት ምንድነው? አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?
እንግዲህ ሁልጊዜ ሲባል የምንሰማው አንድ ሚሊዮን ብር ላወጣ ክለብ ፌዴሬሽኑ አስር ሺህ ብር ሸለመ እየተባለ ይወራል። ሽልማት ማለት ለሰራው ነገር እውቅና እና ክብር መስጠት ነው። እኛ ከፍተኛ ገንዘብ ለሚያወጡ ክለቦች የሚመልስ ገንዘብ መስጠት አንችልም አቅማችንን መታወቅ አለበት። ሆኖም ስፖንሰር በማፈላለግ የተሻለ የሽልማት አይነት እና ከፍ ያለ የገንዘብ መጠን ለመስጠት እየጣርን እንገኛለን። ሽልማቱንም ሜዳ ላይ ከምንሸልም በተሻለ ቦታ ላይ አሰባስበን ደረጃውን በጠበቀ ሆቴል ለመስጠት አስበናል፡፡ በዚህም መሰረት ሽልማቱ ሐምሌ 23 የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ…
በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ የምፈልገው አንዳንድ ጊዜ በስፖርት ስፋራ ችግሮች ሊኖሩ እና ሊነሱ ይችላሉ። ሆኖም ሰሞኑን የሚወራው ነገር ጥቂት ሰዎች በፌዴሬሽን ውስጥ የዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች የተወሰኑ የሊግ ኮሚቴ አመራሮች በፈለጉት መንገድ የሚሽሩ እና የሚቀይሩ አሉ የሚባለው ነገር ከእውነት የራቀ ጉዳይ ነው። እኛ የኢትዮዽያ እግር ኳስን ለማሳደግ እየጣርን እንገኛለን። ከሁለት ሊግ ወደ ስድሰት ሊግ በማሳደግ ከፍተኛ ስራ እየሰራን ነው። በምንም መልኩ የተወሰነ ውሳኔን የምናሰቀይርበት አግባብ የለም።