ሽመልስ በቀለ ወደ ጣሊያን ሊያመራ ነው የሚሉ ዘገባዎችን አስተባብሏል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ፔትሮጀት አማካይ የሆነው ሽመልስ በቀለ በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ጣሊያኑ ክለብ ፓርማ ካሊቺዮ ያመራል የሚሉ ዘገባዎች በስፋት ተነግረዋል፡፡

በዋሊያዎቹ ትጥቅ አቅራቢ በሆነው ኤሪያ አመቻችነት ሽመልስ ወደ ሌጋ ፕሮው ፓርማ ሊዛወር ከጫፍ መድረሱን ቢነገርም ተጫዋቹ ዛሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ዝውውሩ ከእውነት የራቀነው ሲል አስተባብሏል፡፡ ፓርማ ባስተናገደው ኪሳራ ምክንያት በ2015 ከጣሊያን ሴሪ አ ወደ ሴሪ ዲ የወረደ ሲሆን በ2016 ወደ ሌጋ ፕሮ ማደግ ችሏል፡፡ በያዝነው የውድድር ዘመንም ከሌጋ ፕሮ ወደ ሴሪ ቢ ለማደግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን እያደረግ ይገኛል፡፡

ሽመልስ ጉዳዮን ከሚዲዎች መስማቱን የተናገረ ሲሆን ከፔትሮጀት ጋር የውል ግዜ እንዳለው ብቻ እንደሚያውቅ ገልጿል፡፡ “ወደ ጣሊያን ሊመራ ነው የሚለውን ወሬ እኔም ከሚዲያ ነው የሰማሁት፡፡ እኔም ሆንኩ ወኪሌ በዚህ ጉዳይ ላይ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ከፔትሮጀት ጋር ቀሪ የሁለት አመት ውል አለኝ ስለዚህም ውሌን አክብሬ ክለቤን እያገለገልኩ ነው” ይላል የቀድሞ የሃዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ፡፡

ሽመልስ በዝውውር ስሙ ሲነሳ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ አይደለም፡፡ በየካቲት ወር ወደ ቻይና አንደኛ ዲቪዚዮን ክለብ ያመራል የሚሉ ያልተጣሩ ዘጋቦዎች በሰፊው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ሽመልስ እና አጥቂው ኡመድ ኡኩሪ ሊጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች በሚቀሩት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ለክለቦቻቸው ለመጫወት ዛሬ ምሽት ወደ ካይሮ ያመራሉ፡፡

ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ፋዩም ላይ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ምስር አል ማቃሳን ዓርብ ሲገጥም ፔትሮጀት ወደ አሌክሳንደሪያ ተጉዞ የካፍ ኮንፌድሬሽን ተሳታፊ ለመሆን ጥረት ከሚያደርገው አል መስሪ ጋር ቅዳሜ ይፋለማል፡፡ ሊጉን ለ39ኛ ግዜ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው አል አሃሊ በ76 ነጥብ ሲመራ ፔትሮጀት በ42 ነጥብ 8ተኛ እንዲሁም ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ32 ነጥብ 13ኛ ነው፡፡

Leave a Reply