የጨዋታ ሪፖርት | ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወራጁ አአ ከተማን አሸንፏል

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ሲጀመር ቻምፒዮን መሆኑን አስቀድሞ ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው አዲስ አበባ ከተማን 3-0 አሸንፏል፡፡

በጨዋታው የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች በግራ እና ቀኝ ቆመው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን በክብር አጅበው የገቡ ሲሆን ቅደዱስ ጊዮርጊስ በደጋፊዎቹ ግሩም ህብረ ዜማ ታግዞ በቀላሉ አሸንፎ ወጥቷል፡፡

የጨዋታው ሁሉም ጎሎች በተቆጠሩበት የመጀመርያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጎል ለማስቆጠር ብዙም መጠበቅ አላስፈለጋቸውም፡፡ በ3ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ አይቮሪያዊው አጥቂ ብሩኖ ኮኔ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ኳስ ከመቀባበል በዘለለ ሰብረው መግባት አልቻሉም፡፡ በ15ኛው ደቂቃ ከነአን ማርክነህ ከቀኝ መስመር የተመቻቸለትን ኳስ ከፍጹም ቅጣት ክልል ጠርዝ መትቶ ዘሪሁን ታደለ ካመከናት ኳስ ውጪም የሚጠቀስ ሙከራ በመጀመርያው አጋማሽ ማድረግ አልቻሉም፡፡

ጨዋታው አንድ ጊዜ ሞቅ አንድ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ በመሀል ሜዳ ላይ ባመዘነ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ33ኛው ደቂቃ ምንያህል ተሾመ ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን ኳስ ብሩኖ ኮኔ ከአአ ከተማ ተከላካዮች በፍጥነት በመቅደም በግራ አግሩ አክርሮ በመምታት ግሩም ጎል አስቆጥሮ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት ማስፋት ችሏል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ብሩኖ ኮኔ ባለፉት 3 ተከታታይ ጨዋታዎች 5 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

በ43ኛው ደቂቃ የጨዋታው ኮከብ የነበረው ብሩኖ ኮኔ ለራምኬል ያመቻቸለትን ያለቀለት ኳስ ራምኬል አስቆጥሮ የጊዮርጊስን መሪነት ወደ 3 አስፍቶ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ጎሎች ባይቆጠሩም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል፡፡ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከርቀት የሚሞክሯቸው ተደጋጋሚ ኳሶች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚያስችላቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ መሀሪ መና በ54ኛው ደቂቃ እና ያስር ሙገርዋ በ73ኛው ደቂቃ ሞክረው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ያወጣቸው እንዲሁም በሊጉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጀመርያ ጊዜ 90 ደቂቃ መጫወት የቻለው አማካዩ ዘካርያስ ከበደ በተመሳሳይ ከርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ነበሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ72ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል የቀኝ መስመር አክርሮ መትቶ ገብ ጠባቂው ያወጣበት እንዲሁም ብሩኖ ኮኔ በ78ኛው ደቂቃ ከመሀሪ መና የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እና በ84ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ ቋሚ ወደውጪ የወጣበት በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 59 ሲያደርስ አዲስና  አበባ ከተማ የሊጉ ግርጌን ይዞ ማጠናቀቁን ያረጋገጠው አአ ከተማ 20 ነጥብ ላይ ረግቷል፡፡

ሊጉ ነገ ሲቀጥል ከፕሪምየር ሊጉ ላለመውረድ የሚታጉጉ ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ፡፡

አርብ ሰኔ 9 ቀን 2009

09:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልድያ (መድን ሜዳ)

09:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ ንግድ ባንክ (አአ ስታድየም)

09:00 አርባምንጭ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (አርባምንጭ)

09:00 ጅማ አባ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ (ጅማ)

09:00 ፋሲል ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ (ጎንደር)

Leave a Reply