በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ተስተካካይ ጨዋታዎች ወልዋሎ እና መቀለ አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 27ኛ ሳምንት ሊካሄዱ መርሀ ግብር ወጥቶላቸው ሳይካሄዱ የቀሩ ጨዋታዎች ሐሙስ ተካሂደው ወልዋሎ ፣ መቀለ ከተማ እና አአ ፖሊስ ድል አስመዝግበዋል፡፡

አዲግራት ላይ ወሎ ኮምቦልቻን ያስተናገደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2-0 በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርገው ጉዞን አጠናክሯል፡፡

በዝናብና ሐይል የቀላቀለ ንፋስ እንዲሁም በወልዋሎ ደጋፊዎች ልዩ የድጋፍ ድባብ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ ወልዋሎ ከመስመር በሚሻገሩ እና ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች አማካኝነት ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡ በአንጻሩ በመከላከል ላይ ያተኮሩት ወሎ ኮምበልቻዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም አይነት ሙከራ ሳያደርጉ ነበር ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ወልዋሎ ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል ሦስት ጊዜ የግቡ አግዳሚ መትቶ የወጣ ሲሆን በተለይ ቴዎድሮስ መንገሻ ፣ እንዳለ ከበድ ፣ መኩሪያ የሱ ፣ አብርሃ ተዓረ እና አብዱሰላም አማን ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፡፡

በ44ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ወደ ግቡ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን የውስጠኛውን ብረት ገጭታ ወደ ግብነት በመቀየር ወልዋሎን ቀዳሚ ማድረግ ቻሎ የመጀመሪያው አጋማሽ በወልዋሎ መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ኮምቦልቻዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው በመጫወት የግብ እድሎች የፈጠሩ ሲሆን የወልዋሎ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ግብ ከመሆን አድኖቸዋል፡፡ በረጅሙ የሚጣሉት ኮሶችን መጠቀም ያልቻሉት ወልዋሎች ከ65ኛው ደቂቃ ጀምሮ ጫና ውስጥ የገቡ በሚመስል ሁኔታ በተደጋጋሚ ጥፋቶችን መስራት እና መውደቅ እንዲሁም የኳስ ፍሰት በቀላሉ ሲበላሽባቸው ተስተውሏል፡፡

ኮምቦልቻዎች ለጥቃት ወደ ወልዋሎ የሜዳ አጋማሽ አመዝነው በሚጫወቱበት ቅፅበት በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከኤፍሬም ጌታቸው ከርቀት የተላከውን ኳስ መኩርያ ደሱ ወደ ግብነት ለውጦ የወልዋሎን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ እና አስደንጋጭ ሙከራ ሳይስተናገድበት በወልዋሎ 2-0 አሸናፊነት ተገባዷል፡፡

 


የምድቡን ሁለተኛ ደረጃ የያዘው መቀለ ከተማ በትግራይ ስታድየም ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ወልዋሎን መከተሉን ቀጥሏል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ የቀድሞ የዳሽን ቢራ ተከላካይ አሌክስ ተሰማ ያሻገረለትን ኳስ ያሬድ ከበደ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሮ መቀለን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስጨብጧል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በወራጅነት ስጋት ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ፖሊስ ባህርዳር ከተማን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ሰብስቧል፡፡ ይርጋለም ማሞ በ87ኛው ደቂቃ የአአ ፖሊስን ብቸኛ የድል ጎል አስቆጥሯል፡፡

ምስጋና

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ኮምቦልቻን ጨዋታ ለመዘገብ ወደ አዲግራት ባመራንበት ወቅት በከተማው ህዝብ እና ክለቡ ለተደረልን መልካም አቀባበል እናመሰግናለን፡፡ በስፍራው ተገኝተን ያጠናቀርናቸው ሌሎች ዘገባዎችን በቀጣይ የምናቀርብ መሆናችንንም በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡

Leave a Reply