የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ወሳኝ 5 ጨዋታዎች ተደርገው ወራጅ የሚሆኑ ሁለት ክለቦች ሳይለዩ ወደ መጨረሻው ሳምንት ተሸጋግረዋል፡፡ አነጋጋገሪ ጉዳዮች ፣ አወዛጋቢ ውሳኔዎች ፣ የደጋፊዎች ቁጣ እና ተጨማሪ ክለቦችን ወደ ወራጅነት ስጋት የጋበዘው የአርብ ጨዋታዎች መርሀ ግብርን ሶከር ኢትዮጵያ ከየስፍራው በነበሩ ባልደረቦቿ አማካኝነት እንደሚከተለው ቃኝታዋለች፡፡
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 2-0 ወልድያ
-ኦምና ታደለ-
ቃሊቲ አከባቢ በሚገኘው መድን ሜዳ ወልዲያን ያስተናገደው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ታግዞ 2-0 በማሸነፍ ላለመውረድ የሚያደርገውን ጥረት ቀጥሏል፡፡ የኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ጨዋታ 9 ሰዓት መጀመር እየተገባው 10 ሰዓት ሊጀመር ችሏል፡፡
ሁለቱም ክለቦች በሰዓቱ በሜዳው ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የፀጥታ አካላት በሜዳው መገኘት በነበረባቸው ሰዓት ባለመቅረባቸው ጨዋታው ሳይጀመር ለአንድ ሰዓት ቆይቷል፡፡ ልክ በተመሳሳይ እንደተካሄዱት አምስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት መደረግ የነበረበት የኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ጨዋታ የፀጥታ አካላት አርፍደው ተገኝተዋል፡፡ የጨዋታው ኮሚሽነር እና ዳኞችም የፀጥታ አካላት ወደ ሜዳ ባለመምጣታቸው በህጉ መሰረት ጨዋታው ማስጀመር አልቻሉም ነበር፡፡ ከወልዲያ ክለባቸው ለማበረታታት የመጡ የእንግዶቹ ደጋፊዎች በሁኔታው የተሰማቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ ተስተውሏል፡፡ በቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ላይ የፀጥታ አካላት ቢገኙም በጨዋታው ወቅት ግን በፍጥነት መገኘት አልቻሉም፡፡ የመድን ሜዳ ደጋፊን ከተጫዋች የሚለይ አጥር ስለሌለውም በጨዋታው የፀጥታ አካላት መኖር አስፈላጊ ነበር፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ 5 ደቂቃዎች ላይ ኤሌክትሪኮች በተጋጣሚያቸውን የሜዳ ክልል ላይ ተጭነው በመጫወት ወደ አደጋ ክልሉ በፍጥነት መድረስ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስውሏል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ተክሉ ተስፋዬ ከሳጥኑ ውጪ በቮሊ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ወልዲያዎች ከ6ኛው ደቂቃ በኃላ ለአጥቂው አንዱአለም ንጉሴ በሚላኩ ረጅም ኳሶች ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ነበር፡፡ በሰባተኛው ደቂቃ ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ በኤሌክትሪክ ግብ ክልል ቀኝ ጠርዝ ያገኘውን ቅጣት ምት ወደ ውጪ ሲወጣ ከደቂ በኃላ ተክሉ አክርሮ የመታውን ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ኤምክሬል ቢሊንጌ ይዞበታል፡፡
በ19ኛው በጥሩ መልኩ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ተክሉ አመቻችቶ በማቀበል አማካዩ ዳዊት በቢሊንጌ መረብ ላይ ኳስን አሳርፎ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ኤሌክትሪኮች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ይበልጥ ተጭነው እና ኳስ ተቆጣጥረው የመጀመሪያው አጋማሽ እስኪጠናቀቅ ተጫውተዋል፡፡
የመድን ሜዳ ኳስን ለማንሸራሸር የተመቸ መሆኑን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች በአንድ ሁለት ቅብብል የወልዲያ የግብ ክልል በቀላሉ ሲደርሱ ታይቷል፡፡ የወልዲያ የተከላካይ መስመርም በኤሌክትሪክ አማካዮች የሚላኩ አደገኛ የተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን በአግባቡ ከግብ ክልላቸውን መመከት አለመቻላቸውን ይበልጥ ለኤሌክትሪኮች ምቾትን የሰጠ ነበር፡፡ በ29ኛው ደቂቃ ዳዊት ኮትዲቯራዊውን አጥቂ ኢብራሂማ ፎፋናን ከግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ሲያገኛን ፎፋና ካሜሮናዊውን ግብ ጠባቂ አልፎ ለመሄድ ሲሞክር ጥፋት ተሰርቶበት የጨዋታው አርቢትር የፍፁም ቅጣት ምት ለኤሌክትሪክ ሰጥተዋል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱን አምበሉ አዲስ ነጋሽ አስቆጥሮ ቡድኑ 2-0 እንዲመራ አስችሏል፡፡
ከእረፍት መልስ የኤሌክትሪክ የመሃል ሜዳ ብልጫ የቀነሰ ሲሆን ተመጣጣኝ ፉክክር በሁለቱም ክለቦች በኩል ታይቷል፡፡ ወልዲያ ግብ ለማስቆጠር የተጫዋች ቅያሪን ቢያደርግም በሁለቱም ክለቦች በኩል የተደረገው የግብ ሙከራ ግን አነስተኛ ነበር፡፡ በ57ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ጫላ ድሪባ በጥሩ መልኩ የሞከረውን ኳስ የኤሌክትሪኩ ጋናዊ ግብ ጠባቂ አቡ ሱሌማን አምክኖበታል፡፡ በ70ኛው ደቂቃ ሙልጉታ ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም ከደቂቃ በኃላ ተክሉ የሞከሯቸው ሙከራዎች ሌሎች የሚጠቀሱ የግብ ማግባት እድሎች ነበሩ፡፡
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ የወልዲ አማካዮች በሚሰሩት ስህተቶች ምክንያት የአሌክትሪኮቹ ፍፁም እና ፎፋና ግብ የማስቆጠር እድል ቢያገኙም የወልዲያን የተከላካይ ክፍል መስበር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በውጤቱም ኤሌክትሪክ ወልዲያን 2-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡
ድሉን ተከትሎ ኤሌክትሪክ በግብ ክፍያ ጅማ አባ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ በልጦ 12ኛ ሲሆን በሒሳብ ስሌት ወደ ስጋተቱ የገባው ወልዲያ በ34 ነጥብ ባለበት 8ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 ኢትዮጵያ ቡና
-አብርሀም ገብረማርያም-
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረገውን ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አሸንፎ በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ የተመሰረተው የመትረፍ ተስፋውን ወደ መጨረሻ ሳምንት አሸጋግሮ ወጥቷል፡፡
በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በዘንድሮው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል መልኩ በቁጥር አንሰው ስታድየም የተገኙ ሲሆን በክለባቸው እና ተጫዋቾቻቸው ላይ ቁጣቸውን አሰምተዋል፡፡
ቀዝቃዛ ድባብ እና የጨዋታ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት ጨዋታ የተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት የነበራቸው ንግዶ ባንኮች ወደ ቡና የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በዚህ ሒደት በ8ኛው ደቂቃ በቡና የግብ ክልል ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ቢንያም አሰፋ ወደ ግብነት ቀይሮ ሀምራዊ ለባሾቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከጎቡ መቆጠር በኋላም ባንክ አንጻራዊ ብልጫ የወሰደ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ የተላከውን ኳስ ጋብሬል አህመድ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ሞክሮ በሀሪሰን ሄሱ ሲመልሰው የቡና ተከላካዮች ኳሱን በአግባቡ ማራቅ ባለመቻላቸው ቢንያም አሰፋ በግንባሩ በመግጨት ሁለተኛውን አክሎ የመጀመርያው አጋማሽ በንግድ ባንክ 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
እጅግ የተቀዛቀዘ እና የሚጠቀስ እንቅስቃሴ ያልታየበት የሁለተኛው አጋማሽ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከእንቅስቃሴው ይልቅ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ተቃውሞ ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ በተለይም የቡድኑ ተጫዋቾች ላይ በሰማ በታጀበ ተቃውሞ ቁጣቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ላይም በጥላ ፎቅ ፣ ዳፍ ትራክ እና ሚስማር ተራ የተቀመጡ ደጋፊዎች ስታድየሙን ለቀው በመውጣት ይበልጥ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 31 በማድረስ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ ቢቀጥልም ለ18 ተከታታይ የውድድር ዘመናት በቆየበት ሊግ ለመሰንበት በመጨረሻው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ የሌሎችን ውጤት መጠበቅ ይኖርበታል፡፡
ጅማ አባ ቡና 2-0 ሀዋሳ ከተማ
-ዳንኤል መስፍን-
ጅማ ስታድየም ላይ የተደረገው የጅማ አባቡና እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ጅማ አባቡና እጅግ በርካታ ቁጥር በነበራቸው ደጋፊዎቹ ታግዞ በፍፁም የበላይነት 2-0 ማሸነፍ ችሏል።
ከጨዋታው መጀመር አንስተው ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ አባ ቡናዎች ሲሆኑ ከኄኖክ ኢሳይያስ የተቀበለውን ኳስ ሀይደር ሸረፋ 25ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባቡናን ቀዳሚ በማድረግ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ተመሳሳይ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው አባቡናዎች በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ኪዳኔ አሰፋ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ የነበሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን የፍጹም ቅጣት ምት ከሰጡ ኋላ ከረዳት ዳኛው ጋር ተነጋግረው ውሳኔያቸውን መሻራቸው ተቃዉሞ በማስነሳቱ ምክንያት ጨዋታው ለ6 ደቂቃ ያህል ለመቋረጥ ተገዷል፡፡
በ85ኛው ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ ያቀበለውን ኳስ ሱራፌል አወል ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የጅማ አባ ቡናን መሪነት አስተማማኝ አድርጓል። ወደ ጨዋታው መገባደጃ ላይ ሀዋሳዎች ተሽለው የታዩ ቢሆንም ለውጥ ሳይመዘገብ ጨዋታው በጅማ አባቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባቡና በ32 ነጥቦች ከኢትዮ ኤልክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጋር አኩል ነጥብ የሰበሰበ ሲሆን በፕሪሚየር ሊጉ ለመሰንበት ድሬዳዋ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ከወዲሁ አጓጊ አድርጎታል። ሀዋሳ ከተማም ላለመውረድ ከሚታገሉ ክለቦች ጋር ያለው ልዩነት ወደ 2 በመጥበቡ በስጋት ውስጥ ሆኖ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጨረሻው ሳምንት እንዲጫወት አስገድዶታል፡፡
አርባምንጭ ከተማ 0-1 ወላይታ ድቻ
-ቴዎድሮስ ታከለ-
አርባምንጭ ላይ በተደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻ በመጀመርያ ደቂቃ በተገኘች ጎል በማሸነፍ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል ይበልጥ ሲያጠናክር አርባምንጭ ከተማ በአንጻሩ ራሱን ወደ ስጋት ከቷል፡፡
በጨዋታው ሙሉውን ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ክለቦች ለተመልካች ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴን አላሳዩም፡፡ ተደጋጋሚ ሽኩቻዎችም የጨዋታውን ፍሰት ገድበውት ተስተውሏል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ ገና ሁለት ደቂቃ እንዳስቆጠረ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በተከላካይ እና አማካይ ስፍራ እየቀያየረ የሚጠቀመው ፈቱዲን ጀማል ከበዛብህ መለዮ የተቀበለውን ኳስ የአርባምንጭ ተከላካይ ታገል አበበን ስህተት ተጠቅሞ ውድ ሶስት ነጥብ ያስገኘችዋን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከግቧ በኃላ አርባምንጭ ከተማዎች በተለይ በወንድሜነህ ዘሪሁን እነና ገብረሚካኤል ያዕቆብ አማካኝነት የግብ አጋጣሚ በመፍጠር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በጥብቅ መከላከል ተጫውተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደመጀመርያው አጋማሽ አርባምንጭ አቻ ለመሆን የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችልም ወላይታ ድቻ ግቧን አስጠብቆ ለመውጣት አፈግፍጎ በመጫወቱ የግብ እድሎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
አርባምንጭ ከተማዎች በጨዋታው ላይ የተሻለ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ወንድሜነህ ዘሪሁንና እንዳለ ከበደን ቀይረው ማስወጣታቸው በደጋፊው ዘንድ ተቃውሞን አስተከትሎባቸዋል፡፡ በአአ ስታድየም በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንደተደረገው ሁሉ የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎችም በሁለተኛው ዙር እጅግ ደኣማ አቋም ያሳየው ቡድናቸው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል፡፡
ከጨዋታው በኃላ አሰልጣኝ በረከት ደሙ የድህረ ጨዋታ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን የድቻው መሳይ ተፈሪ በድሉ ደስተኛ እንደሆኑና በሚቀጥለው ጨዋታ ትኩረት ሰጥተው በሊጉ መቆየታቸውን እንደሚያረጋግጡ ገልፀዋል፡፡
ወላይታ ድቻ ድሉን ተከትሎ በ33 ነጥቦች በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ሲያለመልም አርባምንጭ ከተማ በተመሳሳይ 33 ነጥቦች በግብ ልዩነት ከድቻ ተሽሎ ተቀምጧል፡፡
ፋሲል ከተማ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ
ጎንደር አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ የተደረገው የፋሲል ከተማ እና የድሬደዋ ከተማ ጨዋታ በእለቱ ብቸኛው አቻ ውጤት የተመዘገበበት ጨዋታ ሆኖ 0-0 ተጠናቋል፡፡
ባለ ሜዳዎቹ ፋሲሎች በጨዋታ እንቅስቃሴም ሆነ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የተሻለ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆኑ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም አብዱራህማን ሙባረክ የግቡ አግዳሚ መለሰበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኗል። በአንፃሩ እንግዶቹ ድሬደዋ ከተማዎች ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ሊያሳይ የሚገባውን ጠንካራ የማሸነፍ ፍላጎት ሳያሳዩ የተሻለ እንቅስቃሴ እንኳን ማድረግ ሲሳናቸው በጨዋታውም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር። ጨዋታውም ምንም ጎል ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት በመጠናቀቅ ነጥብ ተጋርተው ወተዋል ።
የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች በጨዋታው ላይ ዋና ዳኛ የነበሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ላይ ከአንዴም ሁለቴ የፍፁም ቅጣት መስጠት ሲገባቸው አልሰጡንም በማለት ተቋውማቸውን አሰምተዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ወደ 14ኛ ደረጃ የወረደ ሲሆን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት በመጨረሻው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን የማሸነፍ ብቻ ግዴታ ውሰጥ ገብቷል፡፡
ቀሪ ሁለት ወራጆችን የሚለየው የመጨረሻው ሳምንት
የፕሪምየር ሊጉ 30ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የሚካሄድበት ቀን ፣ ቦታ እና ሰአት እስካሁን በፌዴሬሽኑ ያልተገለጸ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማን ተከትሎ የሚወርደውን ቡድን ለመለየት የሚያስችሉ ወሳኝ ጨዋታዎች የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
በሒሳባዊ ስሌት መሰረት 9ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ወልድያ ጀምሮ ሀዋሳ ከተማ ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ወላይታ ድቻ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ጅማ አባ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመውረድ ስጋት ውስጥ ናቸው፡፡
ተጠባቂዎቹ የ30ኛ ሳምንት ፍልሚያዎች
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ድሬዳዋ ከተማ ከ ጅማ አባ ቡና
ወላይታ ድቻ ከ ደደቢት
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ወልድያ ከ አአ ከተማ
ኢትዮጵያ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ
ፋሲል ከተማ ከ አዳማ ከተማ
ሲዳማ ቡና ከ መከላከያ