ኡመድ ኡኩሪ የሊግ ጎል መጠኑን 11 አድርሷል  

በግብፅ 31ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ምስር ኤል ማቃሳ ከኋላ ተነስቶ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን 2-1 መርታት ችሏል፡፡ ከብሄራዊ ቡድን መልስ ክለቡን የተቀላቀለው ኡመድም 11ኛ የሊግ ግቡን አስቆጥሯል፡፡

 

ፋዩም በሚገኘው ፋዩም ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ምስር አል ማቃሳዎች በኳስ ቁጥጥር ከእንግዶቹ ተሽለው ታይተዋል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ኡመድ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን መሪ ያደረገች ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ የምስር አል ማቃሳው አሰልጣኝ ኤሃብ ጋላል በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ቡድናቸው ወደ ጨዋታ እንዲመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ የማቃሳው ተከላካይ አሰም ሰዒድ ከመሃል የተላከውን ኳስ ለማውጣት ጥረት ሲያደርግ ኳስ ኡመድ ጋር ደርሳ በቀላሉ አህመድ መስኡድ መረብ ላይ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ኤል ሃርቢ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል ጥሩ ግብ የማግባት እድልን ቢያገኝም ኦማር ኤል ሰዒድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ይበልጥ ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን በተደጋጋሚም ግብ ለማሰቆጠር ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ማዳጋስካራዊው ፓውሊን ቮቪ በ70ኛው ደቂቃ ማቃሳን አቻ ሲያደርግ በ82ኛው ደቂቃ ጋናዊው ጆን አንቲው ከአሰም ሰዒድ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል፡፡ አንቲው በኢስማኤሊ የተሳካ ግዜን ቢያሳልፍም በሳውዲ አረቢያው አል ሻባብ እና በግብፁ ሃያል ክለብ አል አሃሊ ሳይሳካለት ወደ ምስር አል ማቃሳ ተዛውሯል፡፡

ኡመድ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ግቦች 11 ያደረሰ ሲሆን ይህ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሪከርድ ነው፡፡ ኡመድ ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ክለቡ በአመቱ እንዲያስቆጥር ካስቀመጠለት የግብ መጠን በላይ ኳስን እና መረብ ካገናኘ ዳጎስ ያለ የቦነስ ክፍያ ያገኛል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ያሳየውን ጥሩ እንቅስቃሴ ተከትሎ በግብፅ የሚገኙ እና ከአውሮፓም ጭምር ተጫዋቾቹን ለማዘዋወር ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን ክለቦች ተበራክተዋል፡፡ ኡመድ ከወኪሉ አቡዱልራህማን መግዲ ጋር በመሆን የቀረበላቸውን የዝውውር ጥያቄ እያጤኑ መሆኑን የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊ ገልጿል፡፡

ድሉን ተከትሎ ምስር ኤል ማቃሳ በ67 ነጥብ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማረጋግጥ ሲቃረብ ከመውረድ ስጋት የተላቀቀው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ32 ነጥብ 13ተኛ ነው፡፡ ዛሬ ምሽት 5፡00 ሰዓት የሽመልስ በቀለው ፔትሮጀት አል መስሪን የሚገጥም ይሆናል፡፡ ሊጉ ሊጠናቀቅ ሶስት ጨዋታዎች ቀርተውታል።

የኡመድን ጎል ይመልከቱ | LINK

Leave a Reply