ፕሪሚየር ሊግ ፡ 23ኛ ሳምንት ነገ ይካሄዳል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ነገ ሲካሄዱ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከነማን ፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናግዳሉ፡፡ የመጨረሻዋን የወራጅ ደረጃ ላለመያዝ የሚደረገው ፉክክርም ይቀጥላል፡፡

አበበ ቢቂላ ላይ በ8 ሰአት 5 ጨዋታ እየቀረው ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን በመሆኑ ፤ አርባምንጭ ከነማም ከመውረድ ስጋት ነፃ በመሆኑ ጨዋታው ያን ያህል ወሳኝ ባይሆንም የሁለቱም ደጋፊዎች በብዛት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከሁለቱ ጨዋታ በመቀጠል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመከላከያ 10፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡ ከሴካፋ ናይል ቤዚን ቻምፒዮንሺፕ በሩብ ፍጻሜው ከውድድር የተሰናበተው መከላከያ ከሱዳን መልስ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በመጨረሻዎቹ ተከታታይ ጨዋታዎች ያንሰራሩት መብራት ኃይል እና ዳሽን ቢራ 9፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡ በርካታ የቀድሞ የመብራት ኃይል ተጫዋቾችን (ፌቮ ፣ አስራት ፣ ምንያህል ፣ ሳሙኤል ፣ መስፍን ፣ዮናታን…) የያዘው ዳሽን በአዲስ አባባ ስታድየም ካደረጋቸው የቅርብ ጨዋታዎች በርካታ ነጥቦች የሰበሰበ ሲሆን መብራት ኃይል ደግሞ ያለፉትን 3 ተካታታይ ጨዋዎች በማሸነፍ ከመውረድ ስጋት በመጠኑም ቢሆን እፎይታን አግኝቷል፡፡ ሐረር ሲቲ ከተሸነፈ መብራት ኃይል ከፕሪሚየር ሊጉን አለመውረዱን ለማረጋገጥ ከጨዋታው የአቻ ውጤት ይበቃዋል፡፡

በ11፡30 ኢትዮጵያ ቡና ሙገር ሲሚንቶን ያስተናግዳል፡፡ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ሳይጠበቅ ቡናን ከውድድር ያስወጣው ሙገር የነገውን ጨዋታ በማሸነፍ የመውረድ ስጋቱን ለማስወገድ ይፋለማል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም 2ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ እና የጥሎማለፉን ሽንፈት ለመበቀል ጨዋታውን ይፈልጉታል፡፡

ላለመውረድ ጭላንጭል ተስፋ ያለው ሐረር ሲቲ ወደ ይርጋለም ተጉዞ ሲዳማ ቡናን በሚገጥምበት ጨዋታ ማሸነፍን ብቻ አላማ አድርጎ ይገባል፡፡ ቦዲቲ ላይ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ መድን ወላይታ ድቻን ሲጎበኝ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ ደደቢትን ያስተናግዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *