ፕሪምየር ሊግ ፡ መከላከያ ከ አዳማ ከተማ አቻ ተለያይተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ አንድ ጨዋታ ሲያስተናግድ መከላከያ ከ አዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡

በዝናባማ አየር የተካሄደው ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች መርሀ ግብር ከማሟላት በተለየ ያን ያህል አስፈላጊ አለመሆኑ በሜዳ ውስጥ የታየ በሚመስል መልኩ አንዴ ቀዝቀዝ አንዴ ሞቅ እያለ ተካሂዷል፡፡

በአንጻራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዳማ ከተማ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይ ቡልቻ ሹራ ተቀይሮ ከገባ በኋላ የአዳማ የማጥቃት እንቅስቃሴ መልካም ነበር ማለት ይቻላል፡፡

በ60ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ተከላካዮችን አምልጦ ወደ አዳማ የግብ ክልል በሚያመራበት ወቅት ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ ጎትቶ በማስቀረቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን የተሰጠውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ መትቶ ጃኮ መልሶበታል፡፡

መከላከያ በመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ያገኘውን የቁጥር ብልጫ መጠቀም ያልቻለ ሲሆን ከሳሙኤል ሳሊሶ የተሻገረውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ከወጣበት ኳስ ውጪም የሚጠቀስ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡ አዳማ በአንጻሩ በአዲስ ህንጻ እና ዳዋ ሁቴሳ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር፡፡

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ48 ነጥብ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ በ36 ነጥቦች በነበረበት 7ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል፡፡

Leave a Reply