አዳማ ከነማ በሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ይሳተፋል

ታንዛኒያ በምታዘጋጀው የሴካፋ ክለቦች ካጋሜ ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ አዳማ ከነማ እንደሚሳተፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በሁለተኛ ደረጃነት የጨረሰው ደደቢት በውድድሩ ላይ መሳተፍ ስላልፈለጉ ዕድሉ በሊጉ በሶስተኛ ደረጃነት ለጨረሰው አዳማ ከነማ ተሰጥቷል፡፡ አዳማ ከነማ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ስኬታማ የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡ በሜዳው አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈው አዳማ በሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ሲሳተፍ ይሄ ለሁለተኛ ጊዜው ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ውድድር ላይ ይሳተፋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ሳይሳተፍ ቀርቷል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ አሽኔ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “እኛ ቀድመ ብለን አቋማችን ለፌድሬሽኑ አሳውቀናል፡፡ 3 የውጪ ሃገራት ተጫዋቾችን ብቻ መያዝ በሚለው አዲሱ ህግ ላይ ቅሬታ አለን ለዚህም ሲባል በሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ መሳተፍ አልፈለግንም፡፡ ፌድሬሽኑ እንደአወዳዳሪ አካል በጉዳዩ ላይ ሊያነጋግረን ይገባ ነበር ነገር ግን ይህ አልሆነም፡፡ የሱዳን ጠንካራ ክለቦች አል ሜሪክ እና አል ሂላል በውድድሩ ላይ ባለመገኘታቸው እኛ ይህንን ውድድር ለማሸነፍ አቅደን ነበር፡፡ አዲሱ ህግ ላይ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ላይ መሳተፍ አንፈልግም፡፡”

የታንዛኒያዎቹ አዛም እና ያንጋ አፍሪካ የሱዳኖቹ አልሃሊ ሸንዲ እና ካርቱም አልዋታኒ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ያሳወቁ ሌሎች ክለቦች ናቸው፡፡ አንድም ኢትዮጵያ ክለብ በሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ላይ አሸናፊ ሆኖ አያውቅም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለፍፃሜ በመድረስ ከኢትዮጵያ ክለቦች ብቸኛው ነው፡፡

ያጋሩ