ሀዋሳ ከተማ የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ጥሎ ማለፍ አሸናፊ ሆነ 

የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ አዳማ አበበ ቢቂላ ስቴድየም ላይ በአዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ተካሂዶ ሀዋሳ ከተማ በመለያ ምት በማሸነፍ የድርብ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

ለጨዋታው የተሰጠው ግምት አነስተኛ በሚመስል መልኩ አንድም የፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል በእንግድነት ያልተገኘ ሲሆን በጨዋታው ላይ ታዳጊዎችን ለመመልመል የመጡት የኢትዮዽያ ቡናው አሰልጣኝ ግራጋን ፖፓዲች የዕለቱ የክብር እንግዳ ሆነዋል፡፡ የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴም ተገኝተዋል፡፡

ሁሌም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም በሚደረግ የትኛውም ውድድር የማይቀሩት የአዳማ የስፖርት ቤተሰብ በርከት ብለው በታደሙበት የዛሬው ጨዋታ የአሰልጣኞች ብቃት ሜዳ ላይ የታየበት ጠንካራ ፉክክር ተስናግዶበታል፡፡ ሀዋሳዎች በጉልበት እና ፍጥነት የተሻሉ የነበሩ ሲሆን አዳማዎች በተናጠል የግል ክህሎት እና በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ታይተዋል፡፡

ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በሁሉም የሜዳ ክፍል በሚገባ ኳስን አደራጅቶ በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ጠንካራዎቹ የሀዋሳ ተከላካዮችን አልፈው ጎል ማስቆጠር ተቸግረዋል። በጨዋታው ብልጫ ቢወሰድባቸውም የጎል ሙከራ በማድረግ የተሻሉት ሀዋሳዎች በቸርነት አውሽ አማካኝነት ሁለት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ላይም በዕለቱ  ከቀኝ መስመር እየተነሳ የጎል እድል ሲፈጥር የነበረው ቸርነት አውሽ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ሀዋሳን ቀዳሚ የምታደርግ ጎል አስቆጥሯል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ በስነ ልቦናው የተዳከሙ የሚመስሉት አዳማዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል

በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ያደረጉት የተጨዋች ለውጥ ሀዋሳን ሲያዳክም አዳማ ከተማ  ጠንክሮ እንዲቀርብ አድርጎታል፡፡ ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍቶ 50ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ መንግስቴ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምትን ወደ ጎልነት በመቀየር አዳማን አቻ ማድረግ ችሏል።

በቀሩት 40 ደቂቃ ውስጥ አዳማዎች ተጭነው ብልጫ ወስድው የጎል እድል ቢፈጥሩም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ እንግዶቹ ሀዋሳዎችም ተጫዋቾች በመቀየር የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ ሙከራ አድርገዋል፡፡

የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት ሀዋሳ ከተማ በግብ ጠባቂው ዳግማዊ ተመስገን ድንቅ ብቃት ታግዞ 7-6 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የጥሎ ማለፉ አሸናፊ ሆኗል። ድሉን ተከትሎም ሀዋሳ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ በተዘጋጀው ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ማከል ችሏል፡፡

አመቱን ሙሉ ጥሩ እነቅስቃሴ በማድረግ ሀዋሳን የሁለት እዮሽ ዋንጫ ባለቤት ካደረጉ ተጨዋቾች ፀጋአብ ዮሴፍ ሲጠቀስ በአዳማ በኩል አምና  ከ17 አመት በታች ውድድር ላይ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው በዘንድሮም ከ20 አመት በታች ቡድኑ ውስጥ ጎል በማስቆጠር ግብ አዳኝ መሆኑን ያሳየው የኋላሸት ፍቃዱ ተስፈኛ ተጫዋችነታቸውን አሳይተዋል።

በ12 ቡድኖች መካከል ሲካሄድ በቆየው የዘንድሮ አመት የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ውድድር እንደ አዳማ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮዽያ ቡና እና መከላከያ ያሉ ቡድኖች ጥሩ ብቃታቸውን እንዳሳዩን ሁሉ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ ፣ ደደቢት ፣ ወጣቶች አካዳሚ ፣ ኢትዮ መድን ከተሳትፎ በዘለለ በሚገባ ራሳቸውን በመፈተሽ በቀጣይ አመት ተጠናክረው ሊቀርቡ ይገባል። በተጨማሪም በዚህ የዕድሜ እርከን ተሳታፊ ያልሆኑ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ቡድን በማዋቀር ይሳተፉ ዘንድ መልክታችንን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ውድድርን በላይነት በማዘጋጀት ፣  በመምራት የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያደረገው ተግባር የሚያስመሰግነው ቢሆንም በቀጣይ አመት በዘንድሮ አመት ውድድር ላይ ያልተሳተፉ ሌሎች የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች በዚህ ውድድር እንዲሳተፉ ጥረት ቢደረግ እና አንዳንድ ቡድኖች ተገቢ ያልሆኑ ተጫዋችን እየተጠቀሙ በመሆኑ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲያደርግ እናሳስባለን።

Leave a Reply