በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 28ኛ ሳምንት ጂንካ ላይ ጂንካ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሀላባ ከተማ 2-1 መሪነት 62ኛው ደቂቃ ላይ በተነሳ የደጋፊ ረብሻ ጨዋታው መቋረጡ የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴም በጨዋታው ዙርያ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሰረት የጂንካ ከተማ ደጋፊ ወደ ሜዳ አጥር ዘሎ በመግባት ግርግር በመፍጠሩ ፣ የቡድኑ አባላትም በእለቱ ዳኛ ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው በጂንካ ከተማ ላይ የ100,000 ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡ በቀጣይ የሚያደርጋቸው ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ከከተማው 100 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ ከተማ እንዲያደርግ እንዲሁም የተቋረጠው ጨዋታ በተመሳሳይ ከ100 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ከተማ ከቆመበት እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ የሚካሄድበት ቦታ እና ቀንም የሊግ ኮሚቴው እንደሚወስን ታውቋል፡፡
በእለቱ በዳኛው ላይ ድብደባ የፈጸሙት አላዛር ዝናቡ እና አብርሀ አባተ እንዲሁም ምክትል አሰልጣኙ ፍስሀ ደረጄ ለአንድ አመት ከእግርኳስ ውድድሮች ሲታገዱ እያንዳንዳቸው የ10,000 ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡