ኢትዮጵያዊው አማካይ ጋቶች ፓኖም ለሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ለመጫወት ዛሬ ፊርማውን አኖሯል፡፡ የተጫዋቹ ወኪል ዴቪድ በሻ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ጋቶች የሶስት ዓመት ውል ለማካቻካላ ከተማው ክለብ ለመጫወት ተስማምቷል፡፡
ጋቶች ከሳምንት በፊት ወደ ሩሲያ አቅንቶ የሙከራ ግዜ እያሳለፈ ይገኝ የነበረ ሲሆን የሙከራ ግዜው የአንዚ ክለብ አሰልጣኞችን ያስደሰተ በመሆኑ ተጫዋቹን ለማስፈረም በቅተዋል፡፡ የክለቡ ፕሬዝደንት በፊፋ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሃገራቸው ሩሲያ ከኒውዝላንድ ያደረገችውን የመክፈቻ ጨዋታ ለመታደም ወደ ሞስኮ አምርተው ስለነበር የጋቶች እና አንዚ ዝውውር ጉዳይ ዘግይቶ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሙሉ ለሙሉ ተጫዋቹ የአንዚ ንብረት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ዴቪድ በዝውውሩ እጅግ መደሰቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ “በጣም ደስተኞች ነን፡፡ የሶስት አመት ውል ነው የተፈራረመው፡፡ ጥሩ አቅም ያለው ልጅ በመሆኑ ዝውውሩ እንደሚሳካ እርግጠኞች ነበርን ብሏል፡፡ ይህ ዝውውር ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በር ከፋች እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡”
አንዚ ማካቻካላ ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ስሎቬኒያ ያመራ ሲሆን የቪዛ ጉዳዮችን ጨርሶ አዲሱ ፈራሚ ጋቶችም በቅርቡ እንደሚቀላቀላቸው ይጠበቃል፡፡ ጋቶች በኢትዮጵያ ቆይታው ከታዳጊነቱ ጀምሮ ላሳደገው ኢትዮጵያ ቡና በመጫወት አሳልፏል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዓመትም 8 የሊግ ግቦችን ለቡና ማስቆጠር ችሏል፡፡
*ፎቶ – ዴቪድ በሻ