የጨዋታ ሪፖርት | የፈረሰኞቹ ያለመሸነፍ ጉዞ በኤኤስ ቪታ ተገቷል

በቶታል የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የምድቡን አራተኛ ጨዋታን ለማድረግ ወደ ኮንጎ ያቀኑት ፈረሰኞቹ 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድር ዘመኑ መረባቸው በተደፈረበት ጨዋታም የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባለሜዳዎቹ በተሻለ ኳስን በመቆጣጠር መስርተው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገርግን ከዚህ ቀደም በተለይም በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ እንደሚስተዋለው በመከላከሉ በኩል በተለይም በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ላይ በመጠኑ ተዳክመው መስተዋላቸው ለመጀመሪያዋ ግብ መቆጠር ምክንያት ሆኗዋል፡፡

ባለሜዳዎቹ ኤኤስ ቪታዎች በ7ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በመዘናጋታቸው በመስመሮች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው ያገኙትን ኳስ ሩዋንዳዊዉ አጥቂ ኢኪትያማ አጂቴ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ያደረገችን ኳስ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላም በተደጋጋሚ ቪታዎች ሁለቱን የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮችን በተደጋጋሚ በመፈተን ብሎም አልፈው በመሄድ በተደጋጋሚ ወደ አደጋ ክልል ኳሶሶችን በማድረስ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው ፍሬዘር ካሳ የቪታ ተጫዋቾችን መለያ ይዞ በመጎተቱ የተነሳ ቪታዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኢኪቲያማ አጂቴ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበርካታ አጋጣሚዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መሰንዘሪያ አጋጣሚዎች ቢያገኙም በአመዛኙ ውጤታማ አልነበሩም፡፡ ወደፊት አልፈው በሄዱባቸው አጋጣሚዎችም በቪታዎች በቁጥር ስለሚበለጡ እምብዛም ጥረታቸው ፍሬያማ አልነበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቪታዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመስመሮች በኩል ባደላ አጨዋወት በተደጋጋሚ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከመጀመሪያው በተሻለ በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡

በ54ኛው ደቂቃ ላይ ቪታዎች በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ሆነው ያገኙትን ኳስ አስቻለው ታመነ ነጥቆ በግሩም ሰንጣቂ ሩጫ ወደ ቪታዎች የግብ ክልል ከገቡ በኋላ በኃይሉ አሰፋ ያቀበለውን ኳስ ሰልሀዲን ሰኢድ አግኝቶ የሞከረውን ኳስ የቪታው ግብጠባቂ ያዳነበት ኳስ በፈረሰኞቹ በኩል የተገኘች የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በ55ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሀይሉ አሰፋን አስወጥተው አዳነ ገርማን እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ አለባቸውን አስወጥተው ምንተስኖት አዳነን በማስገባት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ሰቬሪን ከግራ መስመር ሰብሮ ወደ መሀል በመግባት ከቪታዎች የግብ ክልል ውጪ በቀጥታ የመታውን ኳስ የቪታው ግብጠባቂ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስም የሚጠቀስ ነበር፡፡

በ65ኛው ደቂቃ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አዳነ ግርማ ከመሀል ሜዳ በረጅሙ አሳልፎለት ሰልሀዲን ሰኢድ በግሩም ሁኔታ ከቪታዎች የግብ ክልል ጠርዝ እንደነጠረች በቀጥታ በመምታት በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ 7ኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በይበልጥ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም በ77ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ሰቨሬንሆ ከግራ መስመር አታሎ በመግባት ወደግብ የሞከራትን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድን በቅርብ ርቀት የነበረው ናትናኤል ዘለቀ አግኝቶ የሞከራትና ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች፡፡

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዘንድሮው የውድድር ዘመን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከቅድመ ማጣሪያው አንስቶ የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ ከ547 ደቂቃዎች በኋላ መረቡን ሲያስደፍር በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የቻምፒየንስ ሊግ ሽንፈቱንም አስተናግዷል፡፡

በቀጣይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድቡን አምስተኛ ጨዋታ ከወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒየን ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በመጪው ሰኔ 24 ቅዳሜ በ10፡00 በአዲስአበባ ስታዲየም የሚያካሂድ ይሆናል፡፡

1 Comment

Leave a Reply