አርባምንጭ ከተማ ስራ አስኪያጅ እና ቡድን መሪውን  አሰናበተ

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን የመጀመርያ ዙር መልካም ጉዞ ያደረገውና በሁለተኛው ዙር ተዳክሞ በቀጣይ በሊገ የሚቆይበትን እጣ ፈንታ የሚወስን ጨዋታ የፊታችን ቅዳሜ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ሰበታ ላይ ለማድረግ ተገዷል፡፡

ክለቡ በ29ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ተከላካዩ በረከት ቦጋለ በ5 ቢጫ ምክንያት ማረፍ ሲገባው በመሰለፉ ለወላይታ ድቻ ፎርፌ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ የክለቡ የቦርድ አባላት ባደረጉት ስብሰባም በአምስት ቢጫ ማረፍ የሚገባውን ተጫዋች ከማሰለፍ በተጨማሪ በውጤት መጥፋት እና የቡድኑን መንፈስ ባለመጠበቅ ተጠያቂ ያደረጋቸው የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጣሳው ጠቾ እና የቡድን መሪ የሆኑትን ኢ/ር ኢያሱ ላሌቦ ከክለቡ አመራርነት ማንሳቱን ለክለበቡ ቅርበት ካለላቸው ምንጮች ለማወቅ ችለናል።

አርባምንጭ ከተማ በቅርብ አመታት አስተዳደራዊ አለመረጋጋቶች ከሚታዩባቸው ክለቦች አንዱ ሲሆን  አቶ ጣሰው በክለቡ ስራ አስኪያጅነት የተሾሙት በዘንድሮ የውድድር ዘመን ነበር፡፡ ኢ/ር ኢያሱም በክለቡ ቡድነን መሪነት የቆዩት ለ7 ወራት ብቻ ነው፡፡

ክለቡ በተሰናበቱት በዋና ስራ አስኪያጅ እና ቡድን መሪ ምትክ አዲስ የሚመረጡትን ግለሰቦች በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ሲጠበቅ የቀድሞው የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገሌ በጊዜያዊ ቡድን መሪነት እንደተመረጡ ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *