ቻምፒየንስ ሊግ ፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ እና ኤል ሜሪክ ድል ቀንቷቸዋል 

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ማክሰኞ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሲጀመሩ በሜዳቸው የተጫወቱት ቪታ ክለብ፣ ዋይዳድ ካዛብላንካ እና ኤል ሜሪክ ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ኦምዱሩማን ላይ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራን ያስተናገደው ኤክ ሜሪክ ከኃላ ተነስቶ 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የሞዛምቢኩ ክለብ በማኔኤል ፈርናንዴዝ ግብ በ16ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሲሆን ኤል ሳማኒ ሳደልዲን በ32ኛው ደቂቃ ሜሪክን በቅጣት ምት ግብ አቻ አድርጓል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አህመድ ዶፍር ያስቆጠረው ግብ የዲዮጎ ጋርዚያቶን ቡድን አሸናፊ አድርጓል፡፡ ሜሪክ በቻምፒየንስ ሊጉ የመቆየት ተስፋውን ውጤቱን ተከትሎ አለምልሟል፡፡ በጨዋታው ሜሪክ በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የሚችልበትን እድል ባማከናቸው ኳሶች ምክንያት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጨዋታው ኢትዮጵያዊያኖቹ አርቢትሮች ባምላክ ተሰማ፣ ክንዴ ሙሴ፣ ሃይለራጉኤል ወልዳል እና ለሚ ንጉሴ መርተውታል፡፡ ድሉን ተከትሎ ኤል ሜሪክ በምድብ 1 ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

ኪንሻሳ ላይ ኤኤስ ቪታ ክለብ የቅዱስ ጊዮርጊስን የ7 ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞ ገቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በተደጋጋሚ ቀደ ፈረሰኞቹ የግብ ክልል መድረስ የጫሉት ባለሜዳዎቹ በሩዋንዳዊው ዳዲ ቢሮሬ ግብ ቀዳሚ ሲሆኑ በ28ኛው ደቂቃ ቢሮሬ በፍፁም ቅጣት ምት ሁለተኛውን ግብ አክሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት የተሻለ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በ66ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰዒድ ያስቆጠረው ግሩም ግብ ልዩነቱን ወደ አንድ አጥብቦታል፡፡ ሳላዲን በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠን ወደ 7 ማድረስ ችሏል፡፡ ሳላዲን በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ የምድብ መክፈቻ ጨዋታ ክለቡ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር ያለግብ አቻ ሲለያይ በቅጣት ያልተሰለፈ ሲሆን ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ ውጤቱ የደረጃ ለውጥ ምድቡ ላይ ባያመጣም ቪታ ክለብ የቻምፒየንስ ሊግ ቆይታውን ማራዘም ችሏል፡፡

ካዛብላንካ ላይ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ዋይዳድ ካዘብላንካ አል አሃሊን 2-0 በመርታት ወደ አሸናፊነት መመለስ ችሏል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የኮንጎ ብራዛቪሉ ኢንተርናሽናል ፋብሪስ ኦንዳማ ዋይዳድን ቀዳሚ ሲያደርግ ዋሊድ ኤል ካርቲ በ78ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ዋይዳድ ነጥቡን 6 ቢያደርስም ከመሪው አል አሃሊ እና ዛናኮ ጋር የአንድ ነጥብ ልዩነት አላቸው፡፡

ቀሪ 5 የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ይደረጋሉ፡፡

 

የማክሰኞ ውጤቶች

ኤኤስ ቪታ ክለብ 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ 2-0 አል አሃሊ

ኤል ሜሪክ 2-1 ክለብ ፌሮቫሪዮ ደ ቤይራ

 

የዛሬ ጨዋታዎች

15፡00 – ኮተን ስፖርት ከ ዛናኮ (ኦምኒስፖርትስ ሩምዴ አዲያ)

22፡00 – አል ሂላል ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (አል ሂላል ስታዲም)

22፡00 – ዩኤስኤም አልጀር ከ ዛማሌክ (ስታደ ጁላይ 5 1962)

22፡00 – ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)

22፡00 – አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ካፕስ ዩናይትድ (ስታደ አልጠይብ አልማራ)

Leave a Reply