የካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ማክሰኞ መደረግ ሲጀምሩ በሜዳቸው የተጫወቱት አብዛኞቹ ክለቦች ድል ሲቀናቸው የተጠበቀው የሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ቲፒ ማዜምቤ ጨዋታው ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
ምድብ 1
ሪቨርስ ዩናይትድ ኬሲሲኤን ፖርት ሃርኮርት ላይ አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል፡፡ በያኩቡ ጎዎኖ ስታዲየም በዘነበው ከባድ ዝናብ ሜዳው ለመጫወት አዳጋች ቢመስልም ባለሜዳዎቹ ጨዋታው በተጀመረ የመጀመሪያው ደቂቃ በበርናርድ ኦቮክ ግብ መሪ ሲሆን ፍሬድሪክ ኦቦሜት ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ በ15ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ የዩጋንዳው ቻምፒዮን ኬሲሲኤ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል ጥረት ያደረገ ሲሆን ልማደኛው ጅኦፍሪ ሴሬንኩማ ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው 45 በ2-1 ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ሳይቆጠር ሪቨርስ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡
ቱኒዝ ላይ ክለብ አፍሪካ ከኃላ ተነስቶ የሞሮኮውን ፉስ ራባት 2-1 ረቷል፡፡ የመሃመድ ፋውዚሪ የመጀመሪያ አጋማሽ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ፉስ መሪ ሲሆን በ69ኛው ደቂቃ አሊ ኤል አብዲ የቱኒዚያውን ክለብ አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩ ኢመድ ሜኒአዊ ክለብ አፍሪካን ለድል ያበቃች ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ማክሰኞ የተመዘገቡት ውጤቶች ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚገባውን ቡድን ለመየት ልበልጥ አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አራቱም ክለቦች በእኩል 6 ነጥቦች በግብ ክፍያ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ፉስ ራባት እና ክለብ አፍሪካ ምድቡን መሪ ሲሆን ሪቨርስ ዩናይትድ እና ኬሲሲኤ 3ተኛ እና 4ተኛ ናቸው፡፡
ምድብ 2
ኤምሲ አልጀር ምባባኔ ስዋሎስን 2-1 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡ የሂሻም ኒኮቺ የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለት ግቦች ኤምሲ አልጀርን ቀዳሚ ሲያደርጉ ንጃቡሎ ንዶሎቩ ምባባኔን ከመሸነፍ ያላዳነች ግብ በድንቅ ሁኔታ በሁለተኛው 45 ፋውዚ ካውቺ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ የአልጄሪያው ክለብ ምድቡን በ8 ነጥብ መምራት ጀምሯል፡፡
ምድብ 3
ካሉሉ ላይ ዜስኮ ዩናይትድን ያስተናገደው ሬክሬቲቮ ሊቦሎ 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የኮንጎ ብራዛቪሉ ጁልሲ ቡካማ ካያ ሁለት ግቦችን ዜስኮ መረብ ላይ ሲያሳርፍ ፋብሪሲዮ ቀሪዋን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ በሊቦሎ የተወሰደበት ዜስኮ ዩናይትድ በጨዋታው የረባ እንቅስቃሴ ሳያደርግ ጨዋታው ተጠናቅቋል፡፡
አባያድ ላይ አል ሂላል ኦባያድ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ የግቡፁን ስሞሃን 2-1 ረቷል፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ሂላል ኦባያድ በአቡበከር ጊሪፋ ግብ ቀዳሚ ሲሆን ኢስላም ሞአሬብ ስሞሃን አቻ አድርጓል፡፡ ጋናዊው ኔልሰን ላድ ዛጋላ የሂላል ኦባያድን ድል ያረጋገጠች ግብ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ምድቡን አል ሂላል ኦባያድ በ7 ነጥብ ሲመራ ሬክሬቲቮ ሊቦሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ምድብ 4
የጊኒው ሆሮያ የጋቦኑን ሞናናን 1-0 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት ከሱፐርስፖርት ዩናይትድ ተቀብሏል፡፡ ሴኮ አማዱ ካማራ የሆሮያን የድል ግብ በ81ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ሞናናዎች ለአብዛኛው ደቂቃ በጠንካራ መከላከል ሆሮያዎች ግብ እንዳያስቆጥሩ ቢገዱባቸውም የካማራ ግብ ለኮናክሬው ክለብ ሶስት ነጥብ እንዲገኝ አስችላለች፡፡
ፕሪቶሪያ ላይ የተጠበቀው ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ቲፒ ማዜምቤ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ የወቅቱ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊው ማዜምቤ ከባለሜዳዎቹ በተሻለ የግብ እድሎችን መፍጠር ችሏል፡፡ ምድቡን ሆሮያ በ8 ነጥብ ሲመራ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ እና ቲፒ ማዜምቤ በ7 ነጥብ ተከታዮቹን ደረሃች ይዘዋል፡፡
የማክሰኞ ውጤቶች
ክለብ ሬክሬቲቮ ዶስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ 3-0 ዜስኮ ዩናይትድ
ሪቨርስ ዩናይትድ 2-1 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ
ሆሮያ አትሌቲክ ክለብ 1-0 ሲኤፍ ሞናና
ሱፐርስፖርት ዩናይትድ 0-0 ቲፒ ማዜምቤ
ክለብ አፍሪካ 2-1 ፋት ዩኒየን ስፖርት
አል ሂላል አባያድ 2-1 ስሞሃ
ሞውሊዲያ ክለብ 2-1 አልጀር ከ ምባባኔ ስዋሎስ
የዛሬ ጨዋታ
19፡00 – ፕላቲኒየም ስታርስ ከ ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን (ሮያል ባፎኬንግ ስታዲየም)