ጥሎ ማለፍ | ፋሲል ከተማ በመለያ ምቶች አዳማ ከተማን  አሸንፎ ወደ ሩብ ፍጻሜ ተሸጋግሯል

የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በ8:30 በአዲስአበባ ስታዲየም ተካሂዶ ፋሲል ከተማ በመለያ ምቶች አሸንፎ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡

2-2 በተጠናቀቀው መደበኛ ክፍለጊዜ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደግብ በመድረስ ተመጣጣኝ ፉክክርን ማድረግ ቢችሉም ተጠቃሽ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በፋሲል በኩል ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አብዱረህማን ሙባረክና ኤርሚያስ ኃይሉ ወደ ራሳቸው የሜዳ ክፍል በጥልቀት በመመለስ ኳሶችን ከራሳቸው የግብ ክልል በመነሳት እጅግ ፈጣን የሆነ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በጎልህ ፍጥነታቸው በመጠቀም የአዳማ ተጫዋቾችን ሲፈተኑ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ አዳማ ከተማዎች ፊት ላይ ሁለቱ አጥቂዎች ዳዋ ሁቴሳ እና ታፈሰ ተስፋዬነ ከቀሪው የቡድኑ አባላት እጅጉን በመነጠላቸው በተናጥል ተጫዋቾች ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ እንደቡድን በማጥቃቱ ረገድ እጅጉን ደካማ ሆነው ተስተውለዋል፡፡

በ27ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከተማዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ሰለሞን ገ/መድህን የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ያሳለፈለትን ኳስ ወጣቱ አጥቂ አቤል ያለው በቀላሉ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ፋሲሎች ከመጀመሪያው ደቂቃዎች በተለየ በመጠኑ ወደ ኃላ በማፈግፈግ ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገርግን አዳማዎች ይበልጥ ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡ በ36ኛው ደቂቃ ላይም በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ድንቅ የነበረው ቡልቻ ሹራ በግል ጥረቱ ከግብ ክልል ውጪ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት ኳስ የፋሲሉ ግብጠባቂ ቴዎድሮስ ስህተት ታክሎባት ከመረብ ተዋህዳለች፡፡

ከአቻነቷ ግብ መቆጠር በኃላ አዳማ ከተማዎች ፍፁም የበላይነት ወስደው መጫወት ችለዋል፡፡ በተለይም በ39ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ከመስመር ተስፋዬ ነጋሽ ያሻገረለትን ኳስ ሳይጠቀምባት የቀረችው እንዲሁም በ45+1ኛው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ ሞክሮ የግቡ ቋሚ ያዳነበት ኳሶች አዳማን ወደ መሪነት ማምጣት የሚችሉ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሱሌይማን መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ዳዋ ሁቴሳ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ እጅግ በጣም በተቀዛቀዘ መልኩ ሊካሄድ ችሏል፡፡ ፋሲል ከተማ ጎል እሰኪያስቆጥሩ ድረስም ሙከራ አልታየም፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ሀይሉ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከመሃል የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ በመምታት የጃኮ ፔንዜ ግብ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በቀጥታ በመምታት ማራኪ ግብን አስቆጥሮ ጨዋታው 2-2 በሆነ ውጤት በመደበኛ ሰአት ተጠናቆ ወደ መለያ ምት እንዲያመሩ አስችሏል፡፡

በተጨማሪ ደቂቃ ላይ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ ኮነንጓዊው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜን አስወጥተው ጃፋር ደሊልን ሲያስገቡ በአንጻሩ ፋሲል ከተማዎች ኤርሚያስ ኃይሉን አስወጥተው ኤዶሞ ሆሮሶቪን በማስገባት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ማምራት ችለዋል፡፡ በመለያ ምቱ በአዳማ ከተማዎች በኩል ጃፋር ደሊል ሁለት መለያ ምቶችን ሲያድን በአንጻሩ ቴዎድሮስ ጌትነት ሶስት መለያ ምቶችን በማዳን ለቡድኑ ባለውለታ መሆን ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ፋሲል ከተማ በመለያ ምት 3-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከመጪው ሰኔ 20 ጀምሮ ወደሚደረገው የሩብ ፍጻሜ ውድድር መቀላቀል ችሏል፡፡

 

የሩብ ፍጻሜ መርሀ ግብር

ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009

10:30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ

ረቡዕ ሰኔ 21 ቀን 2009

10:30 ወልድያ ከ ፋሲል ከተማ

ሀሙስ ሰኔ 22 ቀን 2009

08:30 ጅማ አባ ቡና ከ አአ ከተማ

10:30 ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

1 Comment

  1. We are always proud of performanca.fassil kenema will champion .THE EMPERORS.

Leave a Reply