ፕሪምየር ሊግ | ደደቢት በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ ሲዳማ ቡናን አሸንፏል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ በ48 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት ደደቢት እና ሲዳማ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ደደቢት በጌታነህ ከበደ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነጥባቸውን ወደ 51 በማሳደግ በ2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችሉ 23ኛ ግቡን ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ የዮርዳኖስ አባይን ሪከርድ ለመስበር ወይም ለመጋራት ተቃርቧል፡፡

ከሰሞኑ ከተጫዋቾቹ ጋር በደሞዝና መሠል ጥቅማጥቅም ቅራኔ ውስጥ የገቡት ደደቢቶች በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እጅግ ደካማ የሆነን እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል፡፡ እጅግ የተቀዛቀዘ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ አዲስ ግደይ በ27ኛው ደቂቃ ካደረጋቸው ተከታታይ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች በስተቀር ምንም አይነት የግብ ሙከራ አልታየበትም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ ደደቢቶች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በጨዋታው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ የነበረው ጌታነህ ከበደ በ66ኛው ደቂቃ ላይ የሰንደይ ሞቱኩን ስህተት ተጠቅሞ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ የተመለሰችው ኳስ የሚጠቀሰ ነበር፡፡

የጌታነህ ጥረት በ82ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ከመሀል የተላከለትን ኳስ ከመረብ አዋህዶ የግቡን መጠን ወደ 23 ማሳደግ ችሏል፡፡

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢት በ51 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ አሁንም ሲገኙ ግብ አዳኛቸው ጌታነህ ከበደ ከዮርዳኖስ አባይ የ24 ግብ ሪከርድ በአንድ አንሶ በ23 ግብ ታሪክ ለመስራት በመጪው ቅዳሜ ከወላይታ ድቻ የሚደረገውን ጨዋታ የሚጠብቅ ይሆናል፡፡

Leave a Reply