ከፍተኛ ሊግ | ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ ፕሪምየር ሊግ ጉዞውን አጠናክሯል

የኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ 28ኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲከናወኑ ወልዋሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ወደ አንደኛ ሊጉ ያንደረደራቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ወሎ ኮምቦልቻም ከመውረድ ስጋት ነጻ የሆነበትን ድል ማስመዝገብ ችሏል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በመድን ሜዳ ላይ በተከናወነ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ መድንን 2-1 አሸንፏል፡፡ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ በሆኑ የወልዋሎ ደጋፊዎች ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች እንግዶቹ ወልዋሎዎች ተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ተሽለው ታይተዋል። በተለይም በቴድሮስ መንገሻ እና ኢዮብ ታደሰ አማካኝነት ያገኙትን የግብ እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በአንፃሩ ባለ ሜዳዎቹ መድኖች የተወሰደባቸውን ብልጫ ተቆጣጥረው ባደረጉት እንቅስቃሴ 34ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አብይ ቡለቲ ወደ ጎልነት በመቀየር መድንን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

የመጀመርያው አጋማሽ  ጨዋታው ሊጠናቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀረው 43ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ ዳኛ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የሰጡትን የፍጹም ቅጣት ምት መኩርያ ደሱ በመምታት ወደ ጎልነት ቀይሮ ወልዋሎዎችን አቻ በማድረግ የመጀመርያው አገማሽ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ወልዎሎዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም  በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የሚፈጥሩት የማጥቃት መንገዳቸው ተሳክቶላቸው በ2007 ብሔራዊ ሊግ ማጠቃልያ ውድድር ላይ በሀድያ ሆሳህና ማልያ ድንቅ አቋሙን ያሳየውና በወላይታ ድቻ የመሰለፍ እድል አጥቶ ወልዋሎን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የተቀላቀለው ቴዎድሮስ መንገሻ 65ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሮ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ መድኖች ተሽለው ጠንካራ የጎል ሙከራ ቢያደርጉም በወልዋሎ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ ጥረት  እና በጠንካራ መከላከል መሪነታቸውን አስጠብቀው   ጨዋታውን በ2-1 አሸናፊነት አጠናቀዋል፡፡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ በስቴዲዮም የተገኙት የወልዋሎ ደጋፊዎችሕ ድሉን ተከትሎ ወደ ሜዳ በመግባት ደስታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ገልፀዋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የወልዋሎ አሰልጣኝ ብርሃኔ በውጤቱ መደሰታቸውን ገልፀው ጠንካራ የቡድን መንፈስ እና ህብረታቸው እዚህ እንዳደረሳቸው ተናግረው ከባዱን ጨዋታ በድል እንደተወጡ ገልጸዋል፡፡ የቀሩትን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ህልማችንንም እናሳካለን ብለዋል።

በዚሁ ምድብ በተካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች ኮምቦልቻ ላይ በተካሄደው ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ፋሲካ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ሰበታ ከተማን 1-0 በማሸነፍ በሊጉ መቆየቱን ሲያረጋግጥ ቡራዮ ላይ ቡራዮ ከተማ ሱሉልታ ከተማን አስተናግዶ 1 – 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።

ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት አዲስ አበባ ፖሊስን 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ 2 ጨዋታ በሚቀረው የምድብ ሀ አአ ፖሊስ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አክሱም ከተማ በ6 ነጥቦች አንሶ በሊጉ የመቆየት እድሉ የተሟጠጠ ሆኗል፡፡

ዛሬ መካሄድ የነበረበት የአማራ ውሀ ስራ እና መቀለ ከተማ እንዲሁም የባህርዳር ከተማ እና ሽረ እንደስላሴ ጨዋታ ወደ ሌላ ቀን በመዟዟሩ ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል፡፡

Leave a Reply