“ከኢትዮጵያ ጋር በነበረን ጨዋታ ዕድለኞች አልነበርንም” – የሌሶቶው አሠልጣኝ ሲፌፌ ማቴቴ

የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሲፌፌ ማቴቴ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ማግኘት ይገባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

አሠልጣኙ እሁድ በባህርዳር ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ጋዜጠኞችን ለማነጋገር ፈቃደኛ ያልነበሩ ሲሆን ወደሌሴቶ ከተመለሱ በኋላ ግን ለሃገራቸው ሚዲያ መግለጫ ሰጥተዋል። “ከኢትዮጵያ ጋር በነበረን ጨዋታ ዕድል ከኛ ጋር አልነበረችም። ጥሩ ለመጫወት ችለን ነበር፤ ባለፈው ወር በኮሳፋ ዋንጫ ካሳየነው ብቃት እጅግ ተሸለን ተገኝተናል። በመጀመሪያው ግማሽ ያደረግነው እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶም ግብ በማስቆጠር ባለሜዳዎቹን ማስደንገጥ ችለናል፤” ሲሉ የጨዋታውን ሂደት ያስረዱት አሠልጣኝ ማቴቴ ለሽንፈታቸው ዋነኛ መንስኤ በወሳኝ ተጫዋቻቸው ላይ ያጋጠመው ጉዳት እንደሆነ ተናግረዋል። “ነገር ግን በሁለተኛው ግማሽ የጨዋታ እቅዳችንን ለማበላሸት የኢትዮጵያ ቡድን ተጫዋቾች ሆን ብለው በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አማካያችንን ማቡቲ ፖትሎዋኔ በመምታት በጉዳት ተቀይሮ እንዲወጣ አድርገዋል። በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ ብንቀጥልም የፖትሎዋኔ ጉዳት አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሮብናል። በዚህም ምክኒያት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ግቦች በማስተናገድ ለመሸነፍ ተገደናል። እውነት ለመናገር ጨዋታውን ቢያንስ በአቻ ውጤት መጨረስ ነበረብን።”

ሲፌፌ ማቴቴ አምና የቀድሞውን አሠልጣኝ ሌስሊ ኖትሲ በመተካት ቡድኑን ከተረከቡ በኋላ ካደረጓቸው 19 ጨዋታዎች በ3ቱ ማሸነፍ ችለዋል። በስራ ዘመናቸው መጀመሪያ ላይ ኬንያ እና ላይቤሪያን በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም በተከታታይ ያስመዘገቧቸው ሽንፈቶች በቡድኑ አሠልጣኝነት መቀጠላቸውን አጠራጣሪ አድርጎታል። የሌሶቶ እግርኳስ ማህበር በሳምንቱ መጨረሻ በአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ማጣሪያ ከቦትስዋና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የሚሸነፉ ከሆነ አሠልጣኙን ከሃላፊነታቸው ለማንሳት እንደወሰነ ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ያጋሩ