“አፍሪካ በሴቶች እግርኳስ ላይ የበለጠ መስራት አለባት” መስከረም ታደሰ

የአፍሪካ ሃገራት ለሴቶች እግርኳስ እድገት የበኩላቸው ድርሻ እየተወጡ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ምክትል ዋና ፀሃፊ መስከረም ታደሰ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ 

ፈረንሳይ ለምታስተናግደው የአለም የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ለመሳተፍ ፍቃደኛ የሆኑት አፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ 19 ብቻ መሆናቸው አህጉሪቱ አሁንም ለሴቶች እግርኳስ በቂ ትኩረትን እንደማታደርግ አመላካች ሆኗል፡፡ እንደቢቢሲ ዘገባ ከሆነ በ2012 የአለም የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ 24 የአፍሪካ ሃገራት የተሳተፉ ሲሆን አሁን ላይ ቁጥሩ ቀንሷል፡፡ የቁጥር መቀነሱ አንደመስከረም አስተያየት ከሆነ አፍሪካ የሴቶችን እግርኳስ ችላ ማለቷን ያሳያል፡፡ “ለአንዳንድ ፌድሬሽኖች የሴቶች እግርኳስ እንደትልቅ ስራ አይታይም፡፡ በአንዳንድ ፌድሬሽኖች የበጀት ችግሮች ሲከሰቱ ቀድሞ የሚጎዳው የሴቶች እግርኳስ ነው፡፡ በፊፋ ደረጃ የሴቶች እግርኳስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ቢሆንም ይህ ወደ አባል ሃገራትም መውረድ አለበት፡፡”

መስከረም ስትቀጥል “ፌድሬሽኖቹ ብቻ አይደሉም ተጠያቂዎች ፤ ካፍም ፌድሬሽኖች የሴቶች እግርኳስ እድገት ላይ በቂ ትኩረትን ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ አልቻለም፡፡”

የአህጉሪቱ የእግርኳስ አስተዳዳሪ የበላይ አካልም ልክ እንደአባል ሃገራቱ ሁሉ ለሴቶች እግርኳስ የሰጠው አናሳ ግምት ብዙ ግዜ ሲያስተቸው ይስተዋላል፡፡ ካፍ ከፈረንሳዩ ግዙፍ ኩባንያ ቶታል ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ የአፍሪካ ዋንጫ፣ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የገንዘብ ሽልማቶች በእጥፍ አድገዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ሃገር 4 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሲያገኝ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ አሸናፊ ግን 200ሺ ዶላር ብቻ ያገኛል፡፡ የሴቶች ሊግ ውድድርን ያዋቀሩ የአፍሪካ ሃገራት ቢኖሩም ክለቦች በአፍሪካ መድረክ ሊወዳደሩ የሚችሉበትን መድረክ ልክ እንደወንዶች እግርኳስ ሁሉ ካፍ ለመቅረፅ ተቸግሯል፡፡

መስከረም ለወደፊቱ አፍሪካ ሃገራት ለሴቶች እግርኳስ የበለጠ ትኩረትን ከሰጡ ነገሮች እንሚሻሻሉ ያላትን እምነት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ገልፃለች፡፡

Leave a Reply