የቀድሞ ስፖርተኞች የፎቶ አውደርዕይ በዛሬው እለት ተከፈተ

በጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ እንዲሁም በጓደኞቹ ጥረት የተሰባሰቡና ከ1940 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም የቂርቆስና የለገሀር አካባቢ የስፖርት ባለውለተኞችን እንዲሁም የቀድሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችና የተለያዩ የእግርኳስ ክለብ ተጫዋቾች ፎቶ የተካተቱበት በአይነቱ ልዩ የሆነ የፎቶ አውደርእይ በዛሬው እለት ረፋድ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ በሻ እንዲሁም በርካታ የቀድሞ ስፖርተኞች በተገኙበት በአዲስአበባ ትንሿ ስታዲየም ተከፍቷል፡፡

በፎቶ አውደርእይ ላይም ከ1940 ጀምሮ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፣ ቦክስ፣ መረብ ኳስ፣ አትሌቲክስ እንዲሁም ሌሎች ስፖርቶች በብሔራዊ ቡድንም ሆነ በክለብ ደረጃ ታሪክ ሰርተው ያለፉ የሀገር ባለውለተኛ የሆነ ስፖርተኞች ተካተዋል፡፡

ዝግጅቱን ያዘጋጀው ጋዜጠኛ ታሪኬ ቀጭኔ በመክፈቻ ንግግሩ ላይ ይህንን ዝግጅት እንዲያዘጋጅ ለረዱት ጓደኞቹ ለሆኑት ጀማል ከበደና ፀጋስላሴ አረጋዊ (ኮሮኮንች) ምስጋናውን አቅርቦ ይህንን ዝግጅት ለማዘጋጀት ስላነሳሳው ሀሳብ ሲያስረዳ ዝግጁቱ በቂርቆስና አካባቢው ተወልደው ለሰፈር ልጆቻቸው አርአያ ከመሆን በዘለለ በስፖርቱ ዘርፍ በሀገር ደረጃ ባለውለታ የሆኑትን አካላትን ለመዘከር መሆኑን ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም በስፖርቱ ዘርፍ ታሪክን በቅብብሎሽ ለማስቀጠልና በዘርፉ ወደፊት ጥናት ለሚያደርጉ አካላት እንደግብአት በመሆን ታሪክን ለማስተላለፍ ታስቦ መዘጋጀቱንም አውስቷል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ ጁነይዲ ባሻ የዝግጅቱ ዋና አዘጋጅ የሆነው ታሪኬ ቀጭኔ ታሪክን ጠብቆ ለዚህ ትውልድ ለማስተላለፍ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገራችን ያለው ደካማ የሆነ የመረጃ አያያዝ ሳይበገር በግሉ ባደረገው ጥረት ይህን መሰል ታሪክ ለትውልድ በማስተላለፉ በድጋሚ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፤ በመቀጠልም አውደርዕዩ በይፉ መከፈቱን አብስረዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ለተለየው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ለነበረው አሰግድ ተስፋዬ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

ይህ በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለትና በስፖርቱ ዘርፍ ያለውን የመረጃ ክፍተትና የታሪክ ቅብብሎሽ ያስቀጥላል የተባለለት አውደርእይም ከዛሬ አንስቶ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *