‹‹የእሁዱ ጨዋታ እቅዳችን የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ኳስ እንዳይቆጣጠሩ ማድረግ ነው ›› የኬንያው አሰልጣኝ ቦቢ ዊልያምሰን

ስኮትላንዳዊው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቦቢ ዊሊያምሰን ቡድናቸው እሁድ በቻን ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ለመጨረስ የሚያስችል ብቃት እንዳለው ተናግረዋል። አሠልጣኙ “የኬንያ ሊግ ከአፍሪካ ጠንካራ ሊጎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር እንሰማለን። እሁድ ከኢትዮጵያ ጋር በምናደርገው ጨዋታም ይህንን ማሳየት ይኖርብናል።” ሲሉ በኬንያ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ኢትዮጵያን በሜዳዋና በደጋፊዎቿ ፊት በማሸነፍ የበላይነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት። አሠልጣኙ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ጥሩ ተጫዋቾች እንዳሏት እና ለብሄራዊ ቡድኑ ተገቢውን ክብር መስጠት እንዳለባቸው ግን አልደበቁም። “ኢትዮጵያውያኑ ኳስን መሬት አስይዞ በአጭር ቅብብል በመጫወት የተካኑ ናቸው። እሁድ የሚኖረን የጨዋታ እቅድም የኳስ ቁጥጥር እንዳይኖራቸው በማድረግ ጨዋታቸውን ማጨናገፍ ነው። በቻን ረጅም ርቀት ለመጓዝ ጥሩ አጀማመር ማድረግ ግድ ይለናል።”

ስኮትላንዳዊው ቦቢ ዊሊያምሰን በአፍሪካ እግርኳስ ረጅም ዘመን የማሰልጠን ልምድ ያላቸው ሲሆን ከ3 ዓመት በፊት በሱዳን በተደረገው የቻን ዋንጫ ላይም የዩጋንዳ ቡድንን ይዘው ተሳታፊ ነበሩ፤ ምንም እንኳን በ3ቱም ጨዋታ ተሸንፈው ከምድቡ ቢሰናበቱም። የጎር ማሂያ ክለብ ተከላካዮች ሃሩን ሻካቫ በወባ በሽታ እንዲሁም ሙሳ መሃመድ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ምክኒያት በጨዋታው የማይሰለፉ ሲሆን ከዚህ ውጪ ግን አሠልጣኙ ምንም የጉዳት ስጋት እንደሌላቸው ተነግሯል። ኬንያ ባለፈው ሳምንት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ከኮንጎ ብራዛቪል ጋር 1-1 በመለያየት ምድቡን መምራት የጀመረ ሲሆን ይህም ለባህርዳሩ ጨዋታ ሞራል ይሆነዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አሠልጣኝ ዊሊያምሰን ከኮንጎ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተሳተፉ 4 ተጫዋቾችን ይጠቀማሉ ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን ግብ ጠባቂው ቦንፌስ ኦሉዎች፣ የመስመር ተከላካዩ አቡድ ኦማር፣ አማካዩ ኮሊንስ ኦኮዝ (በቅፅል ስሙ ጋቱሶ) እንዲሁም አጥቂው ማይክል ኦሉንጋ በቋሚ አሠላለፍ የመግባት ዕድላቸው የሰፋ ነው። በኬንያ ሊግ በ15 ጨዋታዎች 9 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ የሚገኘው የጎር ማሂያ አማካይ ቪክቶር አሊ አቦንዶ የመሃል ክፍሉን የማደራጀት ሃላፊነት የተጣለበት ሲሆን የኤኤፍሲ ሊዮፓርድሱ ጃኮብ ኬሊ ከማይክል አሉንጋ ጋር በአጥቂ ስፍራ እንደሚሰለፍ ተገምቷል።

የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) በሃገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ውድድር ሲሆን ከ2009 ጀምሮ በየሁለት አመቱ እየተደረገ ይገኛል። 4ተኛው የቻን ዋንጫም በቀጣዩ አመት በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሩዋንዳ አዘጋጅነት ይደረጋል።

ያጋሩ