​ጌታነህ ከበደ ለ16 አመታት የቆየውን የዮርዳኖስ አባይን ክብረወሰን ሰበረ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ በ1990 ከተጀመረ በኃላ  በ1993 የያኔው የመብራት ሀይል በአሁኑ አጠራሩ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ዮርዳኖስ አባይ በአንድ የውድድር ዘመን 24 ግቦችን በማስቆጠር ይዞት የነበረው በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንድ የውድድር አመት ከፍተኛ የግብ ብዛት የማስቆጠር ክብረወሰን በደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ተሰብሯል። ጌታነህ በ23 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ የነበረ ሲሆን በዛሬው እለት ክለቡ ደደቢት በወላይታ ድቻ በተሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ የግብ መጠኑን ወደ 25 በማሳደግ ነው የዮርዳኖስን ክብረወሰን ማሻሻል የቻለው፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ጌታነህ ከበደ ከዚህ ቀደም ታፈሰ ተስፋዬ በሁለት አጋጣሚዎች ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ ፣ አዳነ ግርማ እንዲሁም በራሱ በጌታነህ በ2005 ተሞክሮ ለመሰበር ያልቻለውን ክብረወሰን ዘንድሮ ግን ለማሻሻል ችሏል፡፡

የደቡብ አፍሪካው ቢድቪትስ ዊትስን ለቆ በዘንድሮው የውድድር አመት ጅማሮ ላይ የቀድሞ ክለቡን ደደቢት ዳግም መቀላቀል የቻለው ጌታነህ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር የግብ አካውንቱን በከፈተበት ወቅት በርካቶች የዮርዳኖስ ሪከርድ እንደሚሰብር ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር፡፡

ቅድመ ግምቶች ተሳክተውም ጌታነህ ከበደ በዛሬው እለት ፍጻሜውን ባገኘው የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ክለቡ ደደቢት ወደ ወላይታ ሶዶ አቅንቶ በወላይታ ድቻ 4-2 በተሸነፈበት ጨዋታ ለክለቡ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ለዘመናት ያልተደፈረውን ክብረወሰን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ብቻ 25ግቦችን በማስቆጠር ማሻሻል ችሏል፡፡

1 Comment

  1. Yeah dicha secured the points first then getaneh scored 2 goals. If he needed 4 goals the result would have been 6-4.

Leave a Reply