በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርሀ ግብር ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና ጨዋታ ድሬዳዋን ለከፍተኛ ደስታ ፤ ጅማ አባ ቡናን ለጥልቅ ሀዘን ዳርጎ ተጠናቋል፡፡
ማሸነፍ ብቻ በፕሪምየር ሊጉ ያቆየው የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ተጭኖ ሲጫወት አባ ቡና በጥብቅ የመከላከል አጨዋወት ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡
ፌዴራል ዳኛ ዳዊት አሳምነው በዋና ዳኛ የመሩት ጨዋታ ላይ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ እና ጠንካራ የጎል ሙከራ በማድረግ ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋዎች ከጅማ አባ ቡና የተሻሉ ነበሩ። ለአብነት ያህል 13ኛው እና 17ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ወልዴ የሞከራቸው ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በአንፃሩ እንግዶቹ ጅማ አባቡናዎች ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በመምረጥ አሜ መሀመድን ብቻ ከፊት አድርገው አብዛኛዎቹ ተጨዋቾች ከኳስ ጀርባ በመሆን አጥብቀው ሲከላከሉ አሜ መሀመድ በተለያየ የሜዳው ክፍል ጉልበቱን ፣ ፍጥነቱን በመጠቀም የጎል እድል ለማግኘት ከሚፈጥረው እንቅስቃሴ ውጭ የድሬደዋው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ብዙም ስራ ሳይበዛበት ውሏል ማለት ይቻላል።
የጨዋታው አጋማሽ መጠናቀቂያ 44ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ተጨዋቾች ኳስ በእጅ በመነካቱ ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጠን ይገባል በማለት የዕለቱን ዳኛ በመክበብ ተቋሟቸውን ያሰሙበት መንገድ የጨዋታው አንዱ ክስተት ነበር፡፡
ከእረፍት መልስ በጨዋታ አቀራረብ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመርያው አጋማሽ ምንም የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ባለ ሜዳዎቹ ድሬዎች ጎል ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ባልተደራጀ ሁኔታ በመሆኑ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ነበር።
50ኛው ደቂቃ ላይ በግምት 35 ሜትር እርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ዘነበ ከበደ የመታውን ጀማል ጣሰው እንደምንም ያወጣበት ኳስ ለድሬደዋዎች የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ከዚህ የጎል ሙከራ በኋላ የተነቃቁት ድሬዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሃቅ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ያመከናት የማይታመን አጋጣሚ ነበር።
በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው አባ ቡናዎች የተጨዋች ለውጥ በማድረግ ክፍተታቸውን ለመድፈን ካደረጉት ጥረት በተጓዳኝ ሰአቱ እየገፋ በሄደ ቁጥር የአቻ ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መንገድ ተጨዋቾች ሜዳው ላይ በመውደቅ ሰአት ለማባከን ሲሞክሩ ተስተውሏል።
የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ በደረሰ ቁጥር በስታድየሙ የሚገኘው ተመልካች በሙሉ ማለት ይቻላል በጭንቀት ዝምታ ውስጥ ተውጦ ባለበት ሰአት 81ኛው ደቂቃ ላይ ከድሬደዋ የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ በግራ መስመር ላይ ከኳሷ ፊት የሚገኘው ቢያድግልኝ ኤልያስ ኳሱን በመሸፈን የመልስ ምት ለማሰጠት በሞከረበት ቅፅበት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ወርቁ ከጀርባው ሾልኮ በመውጣት በጥሩ እይታ ሳጥን ውስጥ ነፃ ሆኖ ለቆመው ሐብታሙ ወልዴ አመቻችቶ አቀብሎ ተስፋኛው አጥቂ ሀብታሙ ወልዴ በግሩም ሁኔታ በግራ እግሩ በመምታት በዝምታ ተውጦ የነበረው የድሬደዋ ስቴዲዮም በከፍተኛ የደስታ ድምፅ እንዲናጥ አድርጎታል፡፡
በቀሩት ዘጠኝ ደቂቃ ውስጥ ጅማ አባቡናዎች ጎል ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ተጨዋች በመቀየር የተከላካይ ስፍራቸውን ያጠናከሩት ድሬደዋዎች ውጤቱን በማስጠበቅ የሚፈልጉትን ሦስት ነጥብ በማሳካት 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ለከርሞ በፕሪምየር ሊግ መሰንበታቸውን የሚያረጋግጡበትን ወርቃማ ነጥብ ማግኘት ችለዋል። አሰልጣኝ ገብረ መድን ጅማ አባቡናን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ መሻሻል ያሳዩት ጅማ አባ ቡናዎች መሸነፋቸውን ተከትሎ በፕሪምየር ሊጉ በመጡበት አመት ወደ ከፍተኛ ሊግ በአሳዛኝ ሁኔታ ተሰናባች ሆነዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ተጨዋቾቹ አሰልጣኞቹ በስታድየም የሚገኘት የድሬደዋ ከተማ ደጋፊዎች በደስታ ብዛት በእንባ ሲራጩ በአንፃሩ በርካታ ኪሎ ሜትር አቋርጠው የመጡት ደጋፊዎች የቡድኑ ተጨዋቾች በሀዘን ስሜት ውሰጥ ሆነው ታይተዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዘላለም ሽፈራው
” በጣም ውጥረት የተሞላበት የራሳችንን እድል በራሳችን እድል የምንወስንበት ጨዋታ በመሆኑ ፈታኝ ጨዋታ ነበር፡፡ የማታ ማታ ተሳክቶልን ከጨዋታ ብልጫ ጋር ማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፡፡ ጅማ አባ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው ፤ በመውረዱ አዝናለው፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም እግር ኳስ ነው፡፡”
” ከጎሉ መቆጠር በፊት በጣም ተጨንቄ ነበር፡፡ አሁን አቻ ብንወጣ ምንድነው የሚፈጠረው ፤ ደጋፊው ይህ አይገባውም እያልኩ ባለሁበት ሰአት ጎል ሲቆጠር ደስታዬ ልዩ ነበር፡፡ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆንም ድኛለው”
ገብረመድህን ኃይሌ
” የተሸነፍነው ቀድመን ነው፡፡ የተመደበው ዳኛ ማን እንደሆነ ስናውቅ በስነ ልቦናው አዳክሞናል፡፡ እንደምታውቁት ይህ ዳኛ ድሬደዋን ብዙ አጫውቷል ፤ ይህን ተከትሎ እንዲቀየር ያደረግነው ጥረት ሰሚ አጥቶ ወደ ጨዋታው ገባን፡፡ ተጫዋቾቼም ከፍተኛ ጥፋት እየተሰራባቸው ዝም ይል ነበር፡፡ እነሱም ፍፁም ቅጣት ምት ይሰጥብናል ፣ ቀይ ካርድ እናያለን በማለት በመፍራታቸው አቅማቸውን አውጥተው መጫወት አልቻሉም፡፡ መቼ ነው የኢትዮዽያ እግር ኳስ ከእንደዚህ የለየለት ደባ የሚፀዳው፡፡ በእግር ኳስ ህይወቴ እንደዛሬ የቆሰልኩበት ቀን የለም፡፡ ይህ ቡድን መውረድ የለበትም ነበር፡፡ ብቻ እግር ኳሳችን እንዲህ ሆኖ አይቀርም ይስተካከላል፡፡”