ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀዋሳ ነጥብ ተጋርቶ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌትሪክን ገጥም አንድ አቻ በመለያየት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡

በጨዋታው ሙሉ ክፍለ ጊዜ እምብዛም ሳቢ ያልነበረና ተመልካቹን ያላስደሰተ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በተናጥል ተጫዋቾች በግል ከሚያደርጉት ጥረት ውጪ የሚጠቀስ እንቅስቃሴ አልታየበትም፡፡

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማ ወደ ግብ በመድረስ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም ከዳንኤል ደርቤ የተሻገረለትን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን መትቶ የግቡን አናት ታካ የወጣችው ኳስ የምትጠቀስ ነበረች፡፡

በ15ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ እና ፍሬው ሰለሞን አንድ ሁለት ተቀባብለው ፍሬው ያሻገረውን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ የተነቃቁት ኤሌክትሪኮች ሙሉ በሙሉ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ በተለይ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ ፍፁም ገብረማርያም እና ኢብራሂም ፎፋና የሚፈጥሯቸው አስደንጋጭ የግብ እድሎች ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ የኤሌክትሪክ ጫና በ35ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ታፈሰ ሰለሞን በሀዋሳ ግብ ክልል በኢብራሂም ፎፎና ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ አዲስ ነጋሽ ወደ ግብነት ቀይሮ ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከሙከራዎች ይልቅ ሰጣ ገባዎች የበረከቱበት ነበር፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ከረዳት ዳኞች ጋር በሚፈጥሩት ጭቅጭቅ 4 ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመዞባቸዋል፡፡ ጋዲሳ መብራቴ ከርቀት የሚመታቸው ኳሶች እንዲሁም የኤሌክትሪኩ ኢብራሂም ፍፎና ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀስ ነገር አልተስተዋለም፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት በማስተናገዳቸው ምክንያት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮም በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡

Leave a Reply