ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫ ባነሳበት ጨዋታ ንግድ ባንክ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል

በ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አመት የመጨረሻው የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ የብሩኖ ኮኔ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከፕሪምየር ሊጉ ስታወርድ የቅዱስ ጊዮርጊስን የዋንጫ ስነስርአት አድምቃለች ።

በዝናብ ታጅቦ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ታይቶበታል ። ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ በድል ለማክበር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ጨዋታውን አሸንፎ በሊጉ ለመቆየት በማሰብ ወደጨዋታው መምጣታቸው የተሻለ ፉክክር እንዲያሳዩ ምክንያት የሆነ ይመስላል፡፡

ጨዋታውን በፈጣን የመስመር ጥቃታቸው የጀመሩት ጊዮርጊሶች በ3ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ከተነሳ ኳስ በብሩኖ ኮኔ አማካይነት የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርጉ ሙከራው በግቡ አናት ወጥቶባቸዋል ። ሆኖም ከመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች በኋላ የተነቃቁት ንግድ ባንኮች በ45ቱ ደቂቃ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል ። ነገር ግን የአሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ ቡድን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጊዮርጊሶችን የተከላካይ ክፍል ማለፍ አለመቻሉ አብዛኞቹ ሙከራዎቻቸው ከቆሙ ኳሶች እና በእንቅስቃሴ ደግሞ ከረጅም ርቀት የተሞከሩ እንዲሆኑ አስገድዷል ። በዚህም ረገድ በጨዋታው በመስመር አማካይነት የተሰለፈው ፒተር ንዋድኬ 18 ፣ 31 እና 32ተኛ ደቂቃዎች ላይ እንዲሁም ጂብሪል አህመድ በ16ተኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ሞክረዋቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ሲሆኑ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ከቢንያም አሰፋ የተላከለትን ኳስ ከግቡ ጥቂት ርቀት ላይ የሳተበት አጋጣሚ ቡድኑ በጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ የፈጠረው ብቸኛው ዕድል ሆኖ አልፏል ።

በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ የፊት አጥቂያቸውን ቢኒያም አሰፋን በጉዳት ያጡት ንግድ ባንኮች ጥላሁን ወልዴን በመስመር አማካይነት ቀይረው ፒተር ንዋድኬን በፊት አጥቂነት ቢጠቀሙም በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ተቀዛቅዘው ታይተዋል ። በአንፃሩ አብዛኞቹን የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸውን በማሳረፍ ይህን ጨዋታ ያደረጉት ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅተው ታይተዋል ። በ48ኛው ደቂቃ ላይም በመስመር አጥቂዎቻቸው በበሀይሉ አሰፋ እና ፕሪንስ ሰቨሪን አማካይነት ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ፈረሰኞቹ 63ተኛው ደቂቃ ላይም ከባድ ጥቃት ከፍተው ብሩኖ ኮኔ ያለቀለት አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ ለጥቂት አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን የተመለከትንበት ይህ ጨዋታ በ69ኛው እና በ73 ደቂቃዎች ላይ የጂብሪል አህመድ እና የፕሪንስ ሰቨሪን የረጅም ርቀት ሙከራዎች በግቦቹ ቋሚ ሲመለሱም ያሳየን ሲሆን ፒተር ንዋድኬም ከመሀል ሜዳው በጥቂቱ ከተጠጋው የቅጣት ምት በቀጥታ የሞከረው ኳስ በዘሪሁን ታደለ ዳነበት እንጂ አስገራሚ ግብ ለመሆን የተቃረበ ነበር ማለት ይቻላል ።

ሀዋሳ ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን እያደረገ የነበረው ሌላው ላለመውረድ ይፎካከር የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ 1-1 ውጤት ላይ መሆኑ ንግድ ባንኮች ይህን ጨዋታ ቢያሸንፉ በሉጉ ሊቆዩ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸው የነበረ ቢሆንም ቡድኑ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግብ ማግኘት ሳይችል ቀርቷል ። መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላም ጊዮርጊሶች መሀል ሜዳ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት በሀይሉ አሰፋ ሲያሻማው እና ተቀይሮ የገባው ሳላዲን ባርጌቾ በግንባሩ ሲሞክር ከግቡ አፋፍ ላይ ያገኛትን ኳስ አጥቂው ብሩኖ ኮኔ በማስቆጠር ክለቡን ባለድል ማድረግ ችሏል ።

ሆኖም ተጨዋች ግቡን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ሲገልፅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀያሪ ተጨዋቾች በተቀመጡበት አቅጣጫ በመሄድ ሜዳው ውስጥ በተጨዋችምች መሀል  አምባጓሮ እንዲነሳ አድርጓል። በዚህ አጋጣሚም የንግድ ባንኩ ቢኒያም ሲራጅ በሀይሉ አሰፋን  በግልፅ በሚታይ ሁኔታ በጡጫ መቶ በመጣሉ እንዲሁም ብሩኖ ኮኔ ግርግሩ ለመነሳቱ ምክንያት በመሆኑ ሁለቱም በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ጨዋታውም በዚህ ሁኔታ ፍፃሜውን ሲያገኝ ደካማ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አዲስ አበባ ከተማ እና ከጅማ አባ ቡና ጋር ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እና የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጨዋታውን ለዳኙት አልቢትሮች እንዲሁም የውድድር አመቱ ሻምፒዮን ለሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች የሜዳሊያ ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን የሊጉንም ዋንጫ አቶ ጁነዲን ባሻ  ለቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይ አመራር አቶ አብነት ገ/መስቀል እና ለቡድኑ ተጨዋቾች አስረክበዋል። የክለቡ ተጨዋቾች ፣ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት እና አቶ አብነትም ሜዳውን በመዞር ከደጋፊው ጋር ደስታቸውን በመግለፅ በአጠቃላይ ለ29 ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረበት 1990 ወዲህ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ የሊጉን ክብር የተቀዳጁበትን ቀን አክብረዋል ።

የውድድር አመቱን ክለባቸውን ለየት ባለ አኳሁዋን ሲያበረታቱ የከረሙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችምጽ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በጣለው ዝናብ ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ባሰቡት መልክ በብዛት በስቴድየሙን ክፍሎች ባይገኙም በሂደት ቁጥራቸው በርክቶ የተለመደውን ድጋፋቸውን በማሳየት ከተጨዋቾቹ እና ከአቶ አብነት ጋር ደስታቸውን ሲያከብሩ አምሽተዋል ።


 

1 Comment

Leave a Reply