ድሬዳዋ ከተማን ከመውረድ የታደገው ሐብታሙ ወልዴ 

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ከተማ ደካማ የውድድር ዘመን አሳልፎ በመጨረሻው ጨዋታ ባሳካው 3 ነጥብ ከመውረድ ተርፏል፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ለከርሞ በፕሪምየር ሊግ መቆየቱን ያረጋገጠበትን ብቸኛ ወሳኝ ጎል ያስቆጠረው እና በውድድር ዘመኑ 8 ጎሎችን አስቆጥሮ የወደፊቱ ምርጥ አጥቂ እንደሚሆን ያሳየው ሐብታሙ ወልዴ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

የእግር ኳስ ህይወቱን ሀ ብሎ የጀመረው በተወለደበት ጅማ አጋሮ ነው። በፕሮጀክት ወሰጥ አልፎ ለጅማ ከተማ ሲጫወት የተመለከተው ደደቢት 2003 ላይ ለተስፋ ቡድን ከዛም ለዋናው ቡድን መጫወት ቢችልም ከስድስት ወር በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ልደታ ኒያላ ተዛውሮ በብሔራዊ ሊግ ለሦስት አመት ከተጫወተ በኋላ የእግር ኳስ ህይወቱን ወደተሻለ ምዕራፍ ወደቀየረው ኢትዮዽያ መድን አምርቷል፡፡ በመድን ለሁለት መልካም አመታትን ያሳለፈው ሐብታሙ ዘንድሮ ድሬዳዋ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡

” ሊጉ ይከብደኛል ብዬ ነበር፡፡ በመጀመርያዎቹ ጊዜያትም ተቸግሬ ነበር፡፡ በኋላ ግን እየለመድኩት መጥቼ የተሳካ ጊዜ አሳልፌያለው፡፡” የሚለው ሐብታሙ በ30ኛው ሳምንት ድሬዳዋን በሊጉ የምታቆይ ወሳኝ ግብ ቢያስቆጥርም ጅማ አባ ቡና በመውረዱ እንዳዘነ ይናገራል፡፡

” ጨዋታው በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ በሁለታችንም በኩል ከፍተኛ ተነሳሽነት እና የመሸናነፍ ፍላጎት ታይቷል፡፡ በእኛ በኩል ያገኘናቸውን ኳሶች ወደ ጎልነት ለመቀየር በጣም ታግለን ነበር፡፡ በመጨረሻም ከፈጣሪ ጋር ጎል አስቆጥረን ተሳክቶልን ወጥተናል፡፡ ”

” ለመላው የድሬዳዋ ህዝብ ፣ አብረውኝ ላሉ ተጨዋቾች እና ለእስልምና እምነት ተከታዮች ይህችን ጎል በመታሰብያነት አበርክታለው፡፡ ጎሉን በማስቆጠሬ የተሰማኝን ስሜት በምንም ቃል አልገልፀውም፡፡ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም ነበር፡፡ ሆኖም ጎሉ ሁለት ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡ አንደኛ ጅማ የትውልድ ስፍራዬ ናት፡፡ ጅማ አባ ቡናም እንዲወርድ አልፈልግም ነበር፡፡ በመውረዳቸው በጣም አዝኛለው፡፡ ያም ቢሆን ድሬደዋ ከተማ በእኔ ጎል መትረፉ ከፍተኛ የሆነ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡”

ሐብታሙ ዘንድሮ ያሳየውን አቋም ተከትሎ በቀጣዮቹ አመታት ያንጸባርቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ አጥቂዎች አንዱ ሆኗል፡፡ አቋሙን ጠብቆ ለብሔራዊ ቡድንለመመረጥ እንደሚያልምም ያምናል፡፡

” በድሬዳዋ መጥቼ እንዲህ የተሳካ ጊዜ አሳልፋለው ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡  ህዝቡ በጣም ኳስ የሚወድ ጥሩ ደጋፊ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ደጋፊ ብትለፋ ብትደክም ምንም አይመስልህም፡፡ ከድሬደዋ ጋር በሚቀጥለው አመት በተሻለ ሁኔታ እንቀርባለን ፤ በግሌም በዘንድሮ አመት ያሳየሁትን አቋሜን ጠብቄ በሚቀጥለው አመት የውድድር ዘመን ከዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ ብዙ ጎል በማስቆጠር አቅሜን አሳይቼ ለኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ትልቁ ግቤ ነው” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል ።

1 Comment

  1. ልጁ ለክለቡ ለማልያው ያደረገው የዕለቱ እንቅስቃሴ በጣም አስደስቶኛል ሁሉም ተጫዋች የአገሬ ቡድን ነው ብሎ ታማኝነቱን ጠብቆ ክለቡን ውጤታማ ማድረጉ ያስመሰግንአል አገር እንዳተ ያሉ ብዙ ልጆች ያስፈልጋታል በርታ ራስህን ከጠበክና በደንብ ከሠራ ያሰብክበት ትደርሳለህ ሶከሮችም ልጁን በሚገባ አይታችሁታል በርቱ

Leave a Reply