ቢኒያም በላይ ለሙከራ ወደ ጀርመን ያቀናል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ቢኒያም በላይ ለሙከራ ወደ ጀርመኑ ክለብ ዳይናሞ ደርሰደን ዛሬ ምሽት ያመራል፡፡ አማካዩ ከዚህ ቀደም በጀርመን ቦሩሺያ ሞንቼግላድባህ የሙከራ ግዜ ያሳለፈ ሲሆን በአውሮፓ ቆይታው ክለቡን ማሳመን ከቻለ ወደ በቡንደስሊጋ 2 ለሚጫወተው ክለብ ሊፈርም ይችላል፡፡ የቢኒያምን የሙከራ እድል ያመቻቹት ጀርመናዊው ዩአኪም ፊከርት ናቸው፡፡ ፊከርት በጀርመን መንግስት ድጋፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽንን በቴክኒክ ጉዳዮች እየረዱ የሚገኙ የእግርኳስ ባለሙያ ናቸው፡፡

ቢኒያም እድሉን በማግኘቱ መደሰቱን እና የተሰጠውን እድል በመጠቀም በአውሮፓ የመጫወት ህልሙን ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “የሙከራ ግዜው ለምን ያህል ግዜ እንደሚቆይ አላውቅም፡፡ ዳይናሞ ደርሰደን በሚባል ክለብ ነው የሙከራ ግዜ ለማሳለፍ እድል ያገኘሁት፡፡ በአወሮፓ ሊግ ለመጫወት የሚስችለኝ እድል በመሆኑ ህልሜን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለው፡፡ ከፈጣሪ ጋር ይህንን እድል እንደምጠቀምበት ትልቅ እምነት አለኝ፡፡” ይላል ቢኒያም፡፡

ቢኒያም ትውልድ እና እድገቱ በድሬዳማ ከተማ ሲሆን በአሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ላይ ባሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ የብዙዎችን ቀልብ ለመሳብ ችሎ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን እና በአሰልጣኝ ዩሃንስ የዋሊያዎቹ አለቃ በነበሩበት ወቅት በቅርብ ግዜ የተመለከትነው ተስፋሰጪ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረ አማካይ ነው፡፡

ፊከርት በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ቢኒያም የሙከራ ግዜውን በተሳካ ማሳለፍ የሚችል ከሆነ ለአውሮፓ ክለቦች አቅም ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች እንዳሉ ማረጋገጫ እንደሚሆናቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ቢኒያም በዳይናሞ ደርስደን ለሙከራ ለማድረግ ዛሬ ምሽት ወደ ጀርመን ይጓዛል፡፡ ክለቡ አሁን ላይ በጀርመን ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ቡንደስሊጋ 2) ላይ የሚወዳደር ክለብ ነው፡፡ ለሁለት ሳምንታትም በደርሰደንም የሚቆይ ሲሆን ሌሎች አማራጮችንም ለመመልከት ይህ እድል የሚቀጥመን ይሆናል፡፡ የአሁኑ ሙከራ ባሳለፍነው አመት በሞንቼግላድባህ ካደረገው የሙከራ ግዜ የቀለለ እንደሆነ ነው የማስበው፡፡ ከሙከራው በኃላ ለረጅም ግዜ የሚያቆየውን ቪዛ እንዲገኝ አመቻችተን ሌሎች ክለቦችም እንዲመለከቱት እንደምናደርገ ተስፋ አለኝ፡፡ ተስፋ አለኝ ቢኒያም ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ለአውሮፓ ክለቦች መጫወት እንደሚችሉ አመላካች እንደሚሆን፡፡”

እንደፊከርት ገለፃ ከሆነ ሁለት የጀርመን ክለቦች ቢኒያም በቡድናቸው የሙከራ ግዜ እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ ለበርካታ አመታት በካምቦዲያ፣ ማሊ፣ ኮንጎ፣ ቤኒን እና ሩዋንዳ የሰሩት ፊከርት ከዚህ ቀደም ከ30 በላይ ታዳጊ ተጫዋቾችን በአውሮፓ እግርኳስ ህይወት እንዲመሩ አስችለዋል፡፡ በ1953 እ.ኤአ. በምስራቅ ጀርምን ደርሰደን ከተማ የተመሰረተው በሙሉ ስም ስፖርትማንሻፍት ዳይናሞ ደርሰደን በምስራቅ ጀርምን ዝናን ካተረፉ ክለቦች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ ከበርሊን ግንብ መፍረስ በኃላ ለ4 ዓመታት በቡድንደስሊጋ 1 ቢወዳደርም ከ1995 ወዲህ ወደ ዋናው የጀርመን ሊግ መመለስ ከብዶታል፡፡ በ2016/17 የውድድር ዘመን በቡንደስሊጋ 2 ያሳለፈው ክለቡ በ50 ነጥብ በማስመዝገብ 5ተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች የሙከራ ግዜያት በተለያዩ ክለቦች የማሳለፍ እድልን በቅርብ ግዜያት እያገኙ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም በሩሲያ የነበረውን የሙከራ ግዜ በተሳካ ሁኔታ በማሳለፍ ወደ አንዚ ማካቻካላ ባሳለፍነው ዝውውሩን ሲያጠናቅቅ የቀይ ቀበሮዎቹ ተጫዋቾች የነበሩት ጫላ ተሺታ እና ሚኪያስ መኮንን በቱኒዚያው ሃያል ክለብ ኤትዋል ደ ሳህል የተሳካ ቆይታ ነበራቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *