ዮርዳኖስ አባይ ስለ ጌታነህ ከበደ ሪከርድ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ይናገራል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ወላይታ ድቻ ላይ 2 ጎል ያስቆጠረው ግታነህ ከበደ በ25 ጎሎች በአንድ የውድድር አመት በርካታ ግብ የማስቆጠርን ሪኮርድ ከዮርዳኖስ አባይ ላይ ነጥቋል፡፡ በናሽናል ሴሜንት እየተጫወተ የሚገኘው ዮርዳኖስ ስለ ሪከርዱ ፣ ስለ ድሬዳዋ ከተማ እና ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ያለውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርቷል፡፡

ከየመን ከተመለስክ ወዲህ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትገኛለህ፡፡ እንዴት ተመለከትከው?

የኢትዮጵያ እግርኳስን በቅርበት ለመከታተል እድሉን አግኝቻለው፡፡ ጥሩም ጎን አለው መጥፎ ጎኖች አሉት፡፡ እኔ ካየሁት ግን ብዙ መጥፎ ጎኖቹ በዝቷል፡፡ አንድ ጥሩ ጎን የምለው በገንዘብ ደረጃ ተጨዋቾቹ የሚከፈላቸው ክፍያ ማደጉ ነው። እንደዛም ሆኖ ግን ከገንዘብ ጋር የተያያዙ አስቀያሚ ነገር ነው ያሉት፡፡ በፊት ከገንዘብ ጋር ያልተገናኘ ነገር ስላለው ነው እንደዚህ የሆነው ብዬ አስባለው፡፡ አሁን ያለው ነገር አስቀያሚ ነገር ነው፡፡ እያንዳንዱ ክለብ የሚሄድበት መንገድ ፣ ሜዳ ውስጥ የምትመለከተው እንቅስቃሴ እና የሚመዘገበው ውጤት የክለቡን ማንነት ይገልፀዋል። በክለቦች ላይ ወጥ የሆነ ወቅታዊ አቋም አትመለከትም፡፡ ማን ምን እንደሚሰራ ግልፅ ሆኖ ሜዳ ላይ ታያለህ። በእኔ እምነት ትክክለኛውን መንገድ አብዛኛው ክለቦች ይከተላሉ የሚል እምነት የለኝም። ለወደፊት ሳስብ በጣም ነው የምሰጋው፡፡ ሙስና እግር ኳሱ ውስጥ ገብቷል፡፡ ገና ባላ ደገ እግር ኳሳችን ላይ ይሄ ተጨምሮ ከባድ ነው። እግር ኳሱ እንዲያድግ ከተፈለገ የንፅህና ስራ መሰራት አለበት።

የድሬዳዋ ከተማን የዘንድሮ የውድድር ዘመን ጉዞ እንዴት አየኸው?

እንግዲህ የድሬዳዋ ከተማን እንቅስቃሴ ተመልክቻለሁ፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ነው ብለህ የምትፈርደው ነገር  የለም ፤  ለመናገር ይከብዳል፡፡ ማውራቱም ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም ከሌሎቹ ክለቦች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቢያንስ ክለቡ ምንድነው የሚፈልገው? ውጤት ከሆነ ውጤት እንዴት ነው የሚመጣው? ውጤት ገንዘብ ብቻ ስላወጣህ አይመጣም ፤ ብዙ ስራዎች ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ንፁህ ነገሮች ይጠይቃሉ፡፡ መጥፎ ነገሮችን አስወግደህ ጥሩ ነገሮችን ማሳደግ አለብህ። ክለቡ ውስጥ ጥሩ ባለሙያ አስቀምጠህ ኳሱ የሚፈቅደውን ነገር ብቻ እያደረክ መቀጠል ነው ያለብህ ። ድሬዳዋ ከባለፈው አመት የአሁኑ ቡድኑ ይባስ የወረደ ሆኖ ላለመውረድ የሚጫወት ሆኗል፡፡ ስለዚህ ወደ ፊት ክለቡ ካሉበት ስህተቶች ተምሮ እግር ኳሱ በሚፈልገው መንገድ መጨረሻ ላይ እንዲህ ያለ ጭንቀት ውስጥ ከመግባት የሚሰራውን ስራ በትክክል በጊዜ ሰርቶ ከዚህ አስቀያሚ ነገር ውስጥ ለመውጣት ጥረት ማድረግ አለበት እላለሁ።

በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ለ16 አመታት የቆየ ሪከርድ ይዘህ ነበር…

ደስ ይላል፡፡ ይሄን ያህል አመት ሳይሰበር በመቆየቱ እና ሰው ክብር ሲሰጥህ የሚሰማህ ነገር አለ፡፡ ይህንንም ብቻዬን ሰርቼ ያመጣሁት አይደለም ፤ እነዛን ሁሉ ጎሎች ሳገባ አብረውኝ ይጫወቱ የነበሩት ሁሉ አግዘውኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለው። እግር ኳስ እስከሆነ ድረስ የሆነ አመት ይሰበራል ብዬ እገምት ነበር። ከዚህ በፊት እኮ ለመስበር ተቃርበው ነበር፡፡ ሀያ ሁለት ፣ ሀያ ሦስት አስቆጥረው አንድ ሁለት ጨዋታ ሲቀር ነው ሳይሳካላቸው የቀረው። እስከ ዛሬም መቆየቱ የአጥቂ ችግር ነው ብዬ አልወስድም፡፡ ክለቦች በህብረት የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ በጣም ደካማ ናቸው። ይሄም ደግሞ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ላይ ትልቅ ችግር አለ ብዬ ነው የምወስደው፡፡

ሪከርድህን ስለሰበረው ጌታነህ ከበደ ምን ትላለህ?

ምንም የምለው ነገር ባይኖም እንኳን ደስ አለህ ማለት ነው የምፈልገው፡፡ በእኔ ግምት ይህን ሪከርድ ይሰብራል ብዬ አስብ የነበረው ታፈሰ ተሰፋዬ (2001) 23 ጎል በማስቆጠር ደርሶ የነበረውና ወቅታዊ አቋሙም ጥሩ ስለነበር በእርግጠኝነት በዛ ሰአት ይሰብራል ብዬ አስብ ነበር።

አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ ?

አሁን በከፍተኛ ሊግ በናሽናል ሲሚንት እገኛለሁ፡፡ አንድ የመጨረሻ ጨዋታ ይቀራል፡፡ ከዛ በኋላ ኳሱን የማቆምበት ውሳኔ ላይ እደርሳለው። ሳቆምም እንዲሁ ዝም ብዬ አይደለም ፤ አንድ ሰፋ ያለ ነገር ባማረ ሁኔታ ይህን ያከበረኝን ህዝብ በክብር የምሰናበትበት ፕሮግራም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ መስከረም አካባቢ ይኖራል፡፡ ወደፊት ጊዜው ሲደርስ የበለጠውን የማሳውቅ ይሆናል።

ከእግር ኳስ ከተሰናበትክ በኃላ ምን እንጠብቅ?

አሁን ላይ ሆኜ እንዲህ ነው አልልም፡፡ እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ነው። ምንም ቢሆን ግን ከስፖርቱ አካባቢ አልርቅም ብዬ አስባለው።

3 Comments

Leave a Reply