ጥሎ ማለፍ | መከላከያ ለ5ኛ ተከታታይ አመት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀለ

የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የሩብ ፍጻሜ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር መከላከያ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስን በመለያ ምቶች በመርታት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል፡፡ ጦሩ የጥሎ ማለፍ ስፔሻሊስትነቱን ማሳየትም ችሏል፡፡

በመጠነኛ ዝናብ ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ8ኛው ደቂቃ ሳላዲን በርጊቾ ከመሀል ሜዳ የቀኝ መስመር የይድነቃቸው ኪዳኔን መውጣት ተመልክቶ የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ባሳረፋት ግብ መሪ መሆን ችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ መከላከያ በሙከራ እና በእንቅስቃሴ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የበላይነቱን መውሰድ ችሏል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ በአንድ ሁለት ቅብብል በፍጹም ቅጣት ምት ክልል የግራ መስመር የመታውና ዘሪሁን ያዳነበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡ ባዬ በ35ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ መንገድ ከሳጥኑ ግራ መስመር ግብ አስቆጥሮ መከላከያን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከአቻነት ግቡ መቆጠር በኋላ መከላከያ ኳሱን ተቆጣጥሮ እና ጫና ፈጥሮ በመንቀሳቀስ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳሙኤል ታዬ እና በኃይሉ ግርማ ጋር በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል ከግማሽ ጨረቃ አካባቢ አክርሮ የመታውና ወደ የግቡ አግዳሚን ለትሞ ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው የተቀዛቀዘ መልክ ነበረው፡፡ የግብ እድል ያልተፈጠረበትና የሚቆራረጥ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተስዋለበት የጨዋታ ክፍለጊዜም ነበር፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ከተቆጠሩትም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል፡፡

በተሰጡት የመለያ ምቶች መከላከያ 3-2 በማሸነፍ ወደ ግመማሽ ፍጻሜ መሸጋገሩን አረጋግጧል፡፡ የመጀመርያ ምት የመቱት የቅዱስ ጊዮርጊሱ መሀሪ መና እና የመከላከያው በኃይሉ ግርማ በግቡ አናት ወደ ውጪ የሰደዱ ሲሆን ራምኬል ሎክ እና አቡበከር ሳኒ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከመከላከያ ሌሎች ያመከኑ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ለመከላከያ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሽመልስ ተገኝ ሲያስቆጥሩ ምንተስኖት አዳነ እና ያስር ሙገርዋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥረዋል፡፡

ድሉን ተከትሎ በቅርብ አመታት በጥሎ ማለፉ ምርጥ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው መከላከያ ከ2005 ጀምሮ ባሉት የውድድር ዘመናት በሙሉ (ለተከታታይ 5 አመታት) ለግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችሏል፡፡

Leave a Reply