ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩነቱን ሲያሰፋ ሐረር ሲቲ ብሄራዊ ሊግ ደጃፍ ቆሟል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ ዛሬ ተካሂደው ባልተለመደ መልኩ ሁሉም በመሸናነፍ ተጠናቀዋል፡፡

በአበበ ቢቂላ 8፡00 ላይ አርባምንጭ ከነማን ያስተናገደው ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸንፏል፡፡ ለፈረሰኞቹ የድል ግቦቹን አማካዩ ምንተስኖት አዳነ እና ተቀይሮ የገባው በኃይሉ አሰፋ አስቆጥረዋል፡፡ ይህ ድል ለፈረሰኞቹ በውድድር ዘመኑ 20ኛ ድል ሆኖ ሲመዘገብ የበኃይሉ አሰፋ ግብ ደግሞ 50ኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡ በአበበ ቢቂላ ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ከሴካፋ ውድድር የተመለሰው መከላከያ በኢትዮጵ ንግድ ባንክ 1-0 ተረትቷል፡፡ የንግድ ባንክን የድል ግብ ወሰኑ ማዜ ‹‹ ቀስቴ ›› ከመረብ አሳርፏል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄዱት 2 ጨዋታዎች ሁለት ቡድኖችን ከወራጅነት ስጋት ሙሉ ለሙሉ አላቋቸዋል፡፡ በ9፡00 ዳሽን ቢራን ያስተናገደው መብራት ኃይል በዳሽን ቢራ 2-0 ተሸንፏል፡፡ ለዳሽን ቢራ የቀድሞው የመብራ ኃይል ኮከብ ሳሙኤል አለባቸው እና ጅላሎ ሻፊ ሲያስቆጥሩ ድሉን ተከትሎም ዳሽን ቢራ በቀጣዩ አመት በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡

በ11፡30 በተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ሙገር ሲሚንቶ ጨዋታ ሙገር 1-0 አሸንፎ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡ ለሙገር ብቸኛዋን ግብ ቶክ ጄምስ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ አዲሱ አላሮ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ክልል ላይ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ መድንን 3-0 ሲረታ ሐዋሳ ከነማ ደደቢትን በአንዱአለም ንጉሴ እና አመለ ሚልኪያስ ግቦች 2-1 አሸንፏል፡፡ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ሐረር ሲቲን 3-2 አሸንፎ ደረጃ ውስጥ ገብቶ ለማጠናቀቅ ትግሉን ሲቀጥል ሐረር ሲቲ ወደ ከፍተኛው ብሄራዊ ሊግ ለመውረድ ጫፍ ደርሷል፡፡ 3 ጨዋታ በቀረው ሊግ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ብቸኛ ተፎካካሪ በሆኑት መብራት ኃይል እና ሐረር ሲቲ መካከል የ9 ነጥቦች ልዩነት በመኖሩ የምስራቁ ክለብ ከወዲሁ መውረዱን ያረጋገጠ ይመስላል፡፡

ሊጉን ቅዱ ጊዮርጊስ በ62 ነጥብ ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና በ20 ነጥቦች ርቆ በ42 ይከተላል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ኡመድ ኡኩሪ በ14 ግቦች ይመራል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *