ጥሎ ማለፍ | ወልድያ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቀለ

የኢትየጵያ ጥሎ ማለፍ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ከትላንት ጀምሮ መካሄዳቸውን ቀጥለው ዛሬ 10:30 ላይ ፋሲል ከተማን የገጠመው ወልድያ 2-0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል፡፡

ብዙም ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባልታየበት ጨዋታ በሁለቱም በኩል ክለቦቻቸውን ለመደገፍ ከ600 ኪሎ ሜትሮች በላይ አቆራረርጠው በመጡ ደጋፊዎች ታጅቦ ነበር ጨዋታው የተከናወነው።

ወልደያ ቀዳሚ የሆነበትነን ግብ ለማግኘት ጨዋታው ከጀመረ በኋላ ብዙመ መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡ በ2ኛው ደቂቃ አጥቂው ጫላ ድሪባ የግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት አቋቋም ተመልክቶ በመምታት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡

በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሱት ወልድያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጎሉን ካስቆጠሩ በኃላ ተረጋግተው በሚያገኙዋቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ብቻ ለመጠቀም እና ያገኙትን የመሪነት እድል አስጠብቆ ለመውጣት በሚመስል መልኩ ሲጫወቱ ተስተውሏል። በተቃራኒው ፋሲሎች በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም የጠራ የጎል እድል ሳይፈጥሩ የመጀመሪያ አጋማሹን አጠናቀዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል፡፡ በተለይ 49ኛው ደቂቃ በአምበሉ ታደለ ባይሳ አማካኝነት ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የተሞከረች ኳስ የግቡን አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ለአብነት የምትነሳ የአፄዎቹ ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ነበረች።

በ67ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ከያሬድ ብርሀኑ የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም የወልድያን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ የክለቡ ደጋፊዎችን ያረጋጋች ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

አፄዎቹ በጨዋታው ማገባደጃ አካባቢ ተደጋጋሚ የጎል ማግባት ሙከራዎችን በኤርሚያስ ኃይሉ እና አብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ጨዋታው በወልድያ 2-0 አሸናፊነት ተመልሷል፡፡

ወልድያዎች ድላቸውን ተከትሎ በቀጣይ ወደ ፍጻሜው ለመሸጋገር ጥሎ ማለፉን ተጠቅሞ በተከታታይ ሁለት አመታት ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማለፍ ከቻለው መከላከያ ጋር ሰኔ 28 በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል።

 

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች

ማክሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2009

ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 [2-3] መከላከያ

ረቡዕ ሰኔ 21 ቀን 2009

ወልድያ 2-0 ፋሲል ከተማ

ሀሙስ ሰኔ 22 ቀን 2009

08:30 አአ ከተማ ከ ጅማ አባ ቡና

10:30 ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ያጋሩ

Leave a Reply