የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለቻን ማጣረያ ዝግጅት የሚረዳቸውን የተጫዋቾች ስብስብ ለይተዋል፡፡ በጋና 5-0 ከተሸነፈው ስብስብ መጠነኛ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችም ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ መልካም የውድድር አመት ያሳለፈው ሳምሶን አሰፋ ጥሪ ሲቀርብለት ዋናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ከስብስቡ ውጪ ሆኗል፡፡
በተከላካይ መስመር ቡድኑ በግራ መስመር ከፍተኛ እጥረት እንዳለበት ሲነገር መቆየቱን ተከትሎ 2 ተጫዋቾች በቦታው ተመርጠዋል፡፡ የፋሲል ከተማው አምሳሉ ጥላሁን እና የሀዋካ ከተማው አምበል ደስታ ዮሀንስ ጥሪ የቀረበላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ስዩም ተስፋዬ ፣ አዲስ ተስፋዬ እና ተስፋዬ በቀለ ደግሞ ወደ ጋና ከተጓዙት መካከል የተቀነሱ ተከላካዮች ናቸው፡፡
በአማካይ ስፍራ የጎላ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ሽመልስ በቀለ ለጨዋታው ተገቢ ባለመሆኑ (ቻን ላይ መጫወት የማይችል በመሆኑ) እና ጋቶች ፓኖም በቅርቡ ወደ ሩስያ በማቅናቱ ያልተካተቱ ሲሆን ብሩክ ቀልቦሬ ሌላው ከስብስቡ ውጪ የሆነ ተጫዋቾ ነው፡፡ በነዚህ ምትክ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ በኃይሉ አሰፋ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ምንተስኖት አዳነ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለሞን ሲጠሩ የንግድ ባንኩ ቢንያም በላይ ጥሪ ቢደረግለትም ለሙከራ ወደ ጀርመን በማቅናቱ ሳይካተት ቀርቷል፡፡
በአጥቂ መስመር ላይ ኡመድ ኡኩሪ ለጨዋታው ተገቢ ባለመሆኑ ሲቀነስ በሱ ምትክ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ተተክቷል፡፡
ወደ ጋና ካመሩት መካከል የተቀነሱትን ጨምሮ በዝግጅት ወቅት ከቡድኑ ጋር የነበሩት ተክለማርያም ሻንቆ(አአ ከተማ)፣ አወት ገብረሚካኤል (ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ አሜ መሀመድ (ጅማ አባ ቡና) ፣ አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና) እና ታደለ መንገሻ (አርባምንጭ ከተማ) በዚህ ምርጫ መካተት ያልቻሉ ቢሆንም በቀጣይ በሚኖሩ ምርጫዎች ሊካተቱ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቻን 2018 ማጣርያ ጅቡቲን የሚገጥመው ስብስባቸውን ይዘው በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ ወደ ድሬዳዋ እንደሚያመሩ ሲጠበቅ እንደከዚህ ቀደሙ በርካታ ተጫዋች ጠርተው የሚፈልጓቸውን ከማስቀረት ይልቅ የሚጠቀሙባቸውን ተጫዋቾች ብቻ ይዘው ዝግጅት ለማድረግ እንዳሰቡ ታውቋል፡፡
የተጫዋቾች ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች
ጀማል ጣሰው (ጅማ አባ ቡና)፣ ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ) ፣ ለአለም ብርሃኑ (ሲዳማ ቡና)
ተከላካዮች
አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሳላዲን በርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱልከሪም መሃመድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፣ ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ) ፣ ደስታ ዮሀንስ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)
አማካዮች
ሽመክት ጉግሳ (ደደቢት)፣ ሙሉአለም መስፍን (ሲዳማ ቡና)፣ ጋዲሳ መብራቴ (ሃዋሳ ከተማ) ፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ) ፣ ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ናትናኤል ዘለቀ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ በኃይሉ አሰፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
አጥቂዎች
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አብዱልራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ)፣ ሳላዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)